Saturday, May 25, 2024

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣

ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡

Sunday, October 29, 2023

እኛ

 ዐመት እየጠበቅን ደምቀን እንውላለን፣

ሐዘን ለቆን ሳይሆን ተስፋን እያስቀደምን።

Monday, September 18, 2023

አይቀርም ተኝቶ

 እንኳን ነፋስ መንፈስ

ውቅያኖስ ቢመጣ በመዓበል ታጀቦ
ውሽንፍሩን ይዞ ወጀብ አሰክተሎ፤
መውደዱን ረግጦት አፈርን አልብሶ
ሌላ የሚያስገባ በር ሰጥቶ ለጀቦ
ድፍን ልብ የለኝም የሚቀር ተታልሎ፡፡
All reactions:

Friday, July 16, 2021

ከወዴት ሊመጣ …?


ገና በማለዳ ለማኙ ሳያ* ወፍም ሳይንጫጫ ቀድሞ ከንጋቱ፣
ነቅቶ የሚያነቃን ውርጭ ሳይቆልፈው ስል ሆኖ አንደበቱ፣
“ማን ይሆን ዘነድሮን የሚገኘው አልፎ፤
ከመዓት ከመከራው ከመቅሰፍቱ ተርፎ”
እያንጎራጎረ ሲያዜም እየሰማን ከንፈር እየመጠጥን፣
ሥም ያወጣንለት መጠሪያ ‘ሚሆነው “እብድ ወፈፌ” ብለን፣
መንጋቱ ‘ሚታወቅ ሰማይ መገለጡ ጨለማው ማለፉ፣
በእሱው ዜማ ነበር ሁሌ ‘ሚታወጁ ሰርክ የሚለፈፉ፣
በእሱ እንዳልነበረ ደምቆ የምናየው ተውቦ መንገዱ፣
የተሳለቅንበት ጆሮ የነሳነው የምንለው እብዱ፤
ዛሬ፡-
በተራችን ሁላችንም አብደን ሲጠፋብን መላ፣
እህል እየጠጣን ውኃ ልናላምጥ አኝከን ልንበላ፣
ነፋስም ልንጨብጥ ስናባዝን ስንለፋ፣
ውቅያኖስን ልንጠልቅ ጨርሰን በጭልፋ፣
ዳናው ቢናፍቀን ቢያምረን እንጉርጉሮው፣
ማን አየሁ ሊለን ምን ጅብ እንደበላው?
እናማ
ዜማውን ተውሰን ሥንኝ አሰናኝተን፣
እንዲህ ያለ ለቅሶ እንጉርጉሮ አወጣን፣
ዛሬስ ወዴት ገብቶ ምን ጅብ ቢውጠው ነው ዳናውን ያጠፋ፣
አፋችንን ሆኖ የማይናገረው ምን ሆነን እንዲያይ ነው ካሁኑ የከፋ፣
“ማን ይሆን …” እያለ አይናገር ምነው የማይጮኸው ዛሬ፣
ግድግዳው ተንዶ መጠጊያ ስናጣ ስንከበብ በአውሬ፣

Thursday, August 27, 2020

ማንም ነህ ምንም ነህ (2)

ምናምኒት ነገር እጅህ ላይ ባይገኝ ብታጣ ብትነጣ፣

እሳት ተለቅቆብህ ከቤት ብትሳደድ ሜዳ ብትሰጣ፣

አዝመራህም ነድዶ ጨገሬታ ጠፍቶ ጠኔህም ቢበዛ፣

ዕድል ፊት ብተነሳህ አሳዳጅ የሚሆን ተላትህን ብትገዛ፣

አይክፋህ ወንድሜ፣

በደል አይሰማህ መገፋት መጣልህ ፈፅሞ አያስከፋህ፤

ምክንያቱም፣

አንተ ማለት ለዓለም "ምንም ነህ ማንም ነህ"

 

ወገኔ ነው ያልኸው እምነት ጥለህበት ያደረግኸው ተስፋ፣

ቢሸሽ ቢሸሸግም ርቆ እየሔደ ካይንህ ተተሰውሮ ከጎንህ ቢጠፋ፣

ጊዜ እየታከከ ጉልበት ቢያጎለብት ለውድቀትህ ቢቆም አንተኑ ሊገፋ፣

ብንን ብሎ ቢሔድ ነፋስ እንደገፋው እንደጉም ቀሎ የጣልህበት ተስፋ፣

አይክፋህ ወንድሜ፣

በደል አይሰማህ መገፋት መጣልህ ፈፅሞ አያስከፋህ፤

ምክንያቱም፣

አንተ ማለት ለዓለም "ምንም ነህ ማንም ነህ"

 

የምትገብርለት ዓመት እየጠበቅህ፣

ቆሜያለሁ የሚልህ አንተን ልጠብቅህ፣

ካጥቂዎችህ ቢያብር ደጋግሞ ቢክድህ፣

ዓለም ስለተወህ ዓለም ስለረሳህ፣

አይክፋህ ወንድሜ በደል አይሰማህ፣

 

ይልቅስ፣

ቅስምህን አበርታ መንፈስህን አጽና፣

ቀበቶህን አጥብቅ አንገትህንም አቅና፣

አንተን የሚታደግ አውጪ ከፈተና፣

ከራሥህ በስተቀር ማንም የለምና፤

 

አልያማ፣

ጥረህ ተጣጥረህ ታግለህ ካላሸነፍህ ካልወጣህ አርነት፣

ዝምታህ ብርታቱ መታገስህ ኃይል ሆኖት ጉልበት፣

ሽህ ምንተሸህ ሆኖ ተንጋግቶ ይመጣል፣

የቅስምህ መሰበር ውስጡን ወኔ ሞልቶት፣

ኪሱን ሊያደላድል ሊሞላው የሱን ቤት፣

ትርፉን እያሰላ ሊሸጥ ያንተን ሕይወት፣

ምክንያቱም፣

ራሥህ ለራሥህ መድኃኒት ካልሆንኸው መንፈስህ በርትቶ፣

ደድረህ ካልመከትህ ኃይልህ ተጠራቅሞ ቅስምህም ጎልብቶ፣

ዓለም አይሰማህም ደራሽም የለህም፣

የሚገፋህ እንጂ ደጋፊ አታገኝም፡፡

Wednesday, August 19, 2020

መንገዴን አሳይኝ

ገና ከጅምሩ፣

አንቺ ስትመሪ ስከተልሽ ኖሬ፣

ፍቅር በተባለ ገመድሽ ታስሬ፣

ያመጣኝን መንገድ ዛሬ ሳየው ዞሬ፣

ወከክ ብየ ቀረሁ አንገቴን ሰብሬ፤

መቼስ ለምን ካልሽኝ፡-

አንቺ አንቺን እያለ ተከትሎሽ እግሬ በመንደፋደፉ፣

ተስቦ ተገፍቶ አቀበቱን ወጥቶ ሲደርስ ከአፋፉ፣

በግልምጫሽ ብቻ ልቤ ሲደነግጥ ግፍፍ ሲል ቀልቡ፣

ወኔ እና ተስፋዬ በነፋስ ሽውታ ተንነው ገደል ገቡ፤

እናም፣

መውደድ እና ፍቅር ብርታት እየሰጡ እያሉኝ በል ግፋ፣

የወጣሁት ዳገት ወኔን ተመርኩዤ ታጅቤ በተስፋ፣

መልሶ ለመውረድ ጭንቅ ጥብ ሆኖብኝ የበረታ ዳፋ፣

ቁልቁል ተንደርድሬ ባናቴ እንዳልል ትክል ሔጄ እንዳልደፋ፣

ከተነሳሁበት መልሶ የሚያደርስ መሹለኪያ የሚሆን ከማጥ የሚያወጣ፣

መንገድ ምሪኝ እና ጭንቄን ልገላገል ካስገባሽኝ ዓለም ከሰመመን ልውጣ፡፡

Tuesday, June 23, 2020

ምላስህን አስላ፤ ዐይኖችህን ጨፍን፤ ጆሮህንም ዝጋ!

ዛሬ በአንተ ዘመን አድጎ ተመንድጎ ስለተለወጠ የሰው ልጅ እውቀቱ፣

ጊዜው ስላለፈ ዐለምን ለማወቅ መልፋት መዳከሩ መጽሐፍ መጎተቱ፣

ማሰብ ማሰላሰል፣ መጠየቅ መመርመር ጊዜ እያባከኑ፣

ዝና ‘ማያስገኙ ሐብት አያከማቹ ገንዘብ እየሆኑ፣

ፋሽኑ አልፎባቸው ርቋቸው ሔዶ ጥሏቸው ዘመኑ፣

የሊቅነት ልኩ የአዋቂነት ሚዛን ድፍረት በመሆኑ፣

እውቅና ቀርቶብህ ሹመት እና ዝና፣

ሲያጓጓህ እንዳይኖር መባል የኛ ጀግና፣

ፍለጋህን ትተህ ማሠሡን ብራና፣

ጥያቄ መጠየቅ ሙግትን እርሳና፣

ምን ይሉኝን ንቀህ ጆሮህን ዝጋና፣

ማየት ማመዛዘን ይህ ቢሆን እንዲያ ነው … ማለትን በአንድምታ፣

አራግፈህ ውጣና በምላስህ ከብረህ ትገዛለህ እና ሊቅነትን በአፍታ፣

ውጣ በአደባባይ ማንንም ሳትሰማ ፎክር እና ደንፋ፣

ተጀነን ተንጠርበብ፤ ኮራ ብለህ ተጓዝ ደረትህን ንፋ፣

በዝና ላይ ዝና ክብር እየሰለመህ የምትነዳው ጭፍራ፣

የእውቀትህ ምሥክር ገድልህን ዘርዛሪ ብዙ እንድታፈራ፣

በየአደባባዩ፣ በየቴሊቪዥኑ እንዳሸን በፈላው ተንጎራደድ ወጥተህ በየተራ፣

ስትፈልግ ጩህበት፣ ሲያሻህ ስደብበት በልበ ሙሉነት ማንንም ሳትፈራ፣

ታግለህ ተሰውተህ፣ ያገኘኸው ስኬት ድልህ ስለሆነ፣

አፍን አስከፍቶ ድርሳንን ያዘጋ፤ መዝገብ ያስከደነ፡፡


ተረት

ተረት ልነግራቹ ነው፡፡ በጥሞና አድምጡኝ፡፡

ተረት ተረት፡፡

የመሠረት አላችሁ፡፡

ጥሩ! ተረቱን እንደሚከተለው እተርካለሁ፡፡

በሆነ ጊዜ የሆነ ቦታ ሚስቱን በጥርጣሬ የሚከታተል አንድ ባል ነበረ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ውሽማዋ ከቤቱ ሲወጣ ተመለከተና ዛሬማ የእጁን እሰጠዋለሁ ብሎ ሽመል ይዞ ተከተለው፡፡ ከቆይታ በኋላ ባዶ እጁን ወደቤቱ ተመለሰ፡፡ ሚስቱ ማጀት ውስጥ ነበረችና
“ስሚ አንቺ!” ብሎ ተጣራ፡፡
“እነሆኝ” ስትል መለሰችለት፡፡
“ያ ውሽማሽ እኮ ደበደበኝ”፡፡
“በምን?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“በሽመል” ብሎ መለሰላት፡፡
“ሽመል መያዝ አልለመደበትም ነበር፤ ዛሬ እንዴት ይዞ ወጣ?” አሁንም ጠየቀች፡፡
“እሱማ ሽመል መያዝን ከየታባቱ ያውቅና! የእኔን ሽመል ቀምቶ ነው እንጂ የመታኝ” ሲል መለሰላት፡፡

ተረቴን መልሱ፤ አፌን በዳቦ አብሱ!

Monday, June 22, 2020

እርም ለበላ ትግል ...

ምላስህ ላይ ቆሞ ሲጮህ እየዋላ፣

ትከሻህ ለይ ኾኖ በአንተው እየማለ፣
ስላንተ ሊታገል ድርጅት ፈልፍሎ እንዳሸን የፈላ፣
ብዙ ወገን አለህ ከጉሮሮህ ነጥቆ ሆዱን የሚሞላ፣
በደል ተጠይፎ ጉስቁልናህ ከብዶት፣
በመከራህ አዝኖ ያንተ ሕመም አሞት፣
አማራጭ የሚሆን ሊቀድ ዐዲስ ፈሰስ፣
ጥቃትህን ሊመክት እንባህንም ሊያብስ፣
እያሽሞነሞነ በቃላት ከሽኖ ዲስኩሩን በጆሮህ እያንቆረቆረ፣
ያንተ ወኪል ሆኖ ሲፋጭ እንደሚውል ስላንተ እያረረ፣
አደባባይ ቆሞ ሲሰብክ የሚውለው ተሳደድኩ እያለ የሚብከነከነው፣
የአንተ ማጣት መንጣት እየቆረቆረው ሰቅዞ እየያዘው እረፍት እየነሳው፣
መሆኑን ሲነግርህ ደጋግመህ ስትሰማ፣
የትግሉን መሠረት ዕቅድ እና ዓላማ፣
እምነት ጥለህበት የተነሳህለት ያቆመህ ከጎኑ፣
የምትሰዋለት እሱ በጀመረው በያዘው ውጥኑ፣

ዳግመኛም፡-
ችግርህ ተቀርፎ ትንን ብሎ ጠፍቶ አልፎ ሰቀቀኑ፣
ፋና እንዲበራልህ ጨለማህ ተገፍፎ እንዲነጋ ቀኑ፣
"ከእሱ በፊት እኔ፤ እንዲነጋ ቀኔ፣
ወገቤ እየጠና እንዲደረጅ ጎኔ፣
ግፉ እንዲያበቃልኝ የያዘኝ ኩነኔ፣
ባደግሁበት ምድር መኖር በምናኔ፣
እሱ ይከተለኝ እቀድማለሁ እኔ፣"
ያልህለት ታጋይህ ከመንገዱ ወጥቶ፣
ቆምሁለት ያለውን ዓላማውን ትቶ፣
በስምህ ነግዶ ትርፉን አደርጅቶ፣
ከፍ ከፍ እያለ ዝናው ተንሰራፍቶ፣
ዞሮ የማያይህ ሆኖ ስታገኘው ውለታን የረሳ፣
ትናንቱን ዘንግቶ እንዴትና ለምን የት እንደተነሳ፣
ቅስምህን ቢሰብረው አንጀትህ ቢከስል ቢገኝ ተኮማትሮ፣
አንተው ለራስህ ቁም እሱ ሆዱን እንጂ አያይህም ዞሮ፤

እንጂማ!
ቆሞልኛል ብለህ የምትከተለው፣ ያድነኛል ያለኸው፣
በስምህ የማለው በአንተ የሚገዘተው፣
ጥምህ የሚሰማው መራብህን የሚያየው፣
እርዛትህን ቀርፆ ምስሉን የሚይዘው፣
መሰላሉ ሆኖት እያሸጋገረው ከዙፋን ላይ ወጥቶ፣
አንተኑ ሊበላህ ቀድሞ የጋጠህን እንዳዲስ ተክቶ፣
አመዳይ ሊያለብስህ የእግሩ መርገጫ አርጎ፣
ገትኖ ሊበላህ በአንተው ወዝ አምጎ፣
ካልሆነ በስተቀር፣
እጥፍ ብሎ አንጀትህ መንምነህ እያየህ ሰውነትህ ጫጭቶ፣
ሙግግ ክስት ብለህ የለበስኸው ቆዳህ እላይህ ላይ ለፍቶ፣
ችጋር አንቆ ይዞህ ሆድህ ተሰልቅቦ ከጀርባህ ተጣብቆ፣
ማጣትህ መንጣትህ አደባባይ ወጥቶ ሲውል ፀሐይ ሙቆ፣
ሙቶ ከከረመ አጽሙ አፈር ከሆነ፣
ከዓለም ተሰናብቶ ምእት ከደፈነ፣
ሲሟገት አይውልም አስክሬን ቀስቅሶ፤
አልያም
ግዑዝ ከሆነ አካል ጆሮው ከማይሰማ ከድንጋይ ምሰሶ፣
ሲታከክ አይውልም በድንጋይ ላይ ቆሞ ድንጋይ ተንተርሶ፤
ስለዚህ ወንድም ሆይ!

እሱን ተወውና ልቡናህን አድስ፤ ራስህን አንጽ በራስህ ላይ ሥራ፣
ባንተ ላይ ተራምዶ ወደ ላይ ከወጣ ጆሮውም አይሰማ ደጋግሞ ቢጠራ፡፡

Saturday, June 20, 2020

ዛሬ እንዴት አነሰ?

ትላንት ያወደስነው ስሙን የጠራነው አክብረን በደስታ፣

ዜማ ያዜምንለት ጀግና ነህ እያልነው መጽናኛ መከታ፣

“አብሪ ኮከብ ሆኖ እየተተኮሰ፣

የነጻነት ችቦን ቀድሞ የለኮሰ፣

አጽናፍን አዳርሶ ሥሙ የነገሠ፣

ኩስምን ሁነቶችን ግርማ እያለበሰ፣

ገንኖ እያገነነ ዐለምን መዳፏን አፏ ላይ ያስጫነ፣

ከተናቁት መሀል አስናቂ እንዲወጣ ሠርቶ ያሳመነ፣”

እያልን የካብነውን ከፍ እያደረግን አውጥተን ከማማ፣

ገድየ አሞታለሁ ያልንለት በክፉ ሲነሳ ሲታማ ስንሰማ፤

 

ዛሬ፡-

ካለፈ በኋላ ጉድጓድ ውስጥ ከገባ አፈር ከለበሰ፣

አጥንቱ ከላመ፤ ሥጋው አፈር ሆኖ ገላው ከፈረሰ፣

ዐለም ከረሳችው ከውጣ-ውረዷ ከተሰናበተ፣

በሌለበት ጊዜ፣ መልስ በማይሰጠን እየተሟገተ፣

ከየጥጋጥጉ ጥያቄዎች በዙ የክስ ጎርፍ ጎረፈ፣

አርነት ያወጣ መንገድ እያበጀ ጠርጎ ያሳለፈ፣

እያልን ያወራነው ያ ሁሉ ውዳሴ ያ ሁሉ ሙገሳ፣

ሰውየው ቢጠፋ ከምኔው ተተወ ከምኔው ተረሳ?

ስሙን ያጠቆርነው ጥላሸት የዋጣው ማቅን የለበሰ፣

ከትላንቱ ግብሩ አሁን ምኑ ታጣ? ዛሬ እንዴት አነሰ?


Sunday, June 7, 2020

እንደግመል ሽንት ሁልጊዜም የኋሊት፤ አይሰለችም?

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የጉዞውን መነሻ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ብቅ ባሉት ጋዜጣዎች ጀምሮ በዓይነት እና በቁጥር እየሰፋ ዛሬ ላይ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጋዜጣ ምዕት ዓመት የሞላው ሲሆን የመጀመሪያው ሬዲዮ ጥር 23፣ 1927 ዓ.ም. ሥርጭቱን ከጀመረ 85 ዓመታትን አልፏል፤ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ጣሚያም ሥርጭቱን በ1957 ዓ.ም ከጀመረ 55 ዓመታትን ተጉዟል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ሚዲያ ዛሬ ላይ የተሳካላቸው እና ተጠቃሽ ሚዲያዎች ካሏቸው በርካታ ሀገራት ቀድሞ የተጀመረ መሆኑን ያሳያል፡፡

ዕድሜው የመርዘሙን ያህል ግን ሚዲያው እና ጋዜጠኝነቱ እያደገ ከመምጣት ይልቅ ወደ መጣበት አዙሮ እያየ የኋሊት ጉዞን የመረጠ እንዲመስል አድርጎታል፡፡ በቅርብ ዓመታት በርከት ያሉ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም የሕትመት ሚዲያዎች ተመሥርተውና ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሥራ ቢጀመሩም የሚዲያውን የቀደመ አካሔድ ከማስተካከል እና ጉብጠቱን ከማረቅ ይልቅ ከጉብጠቱ ጋር ተስማምተው መኖርን የመረጡ መሆናቸውን ማንም የሚዲያዎቹ ተካታታይ ይታዘባል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት የአንድ ወገን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎች ሆነው መጡ፣ ዛሬም ቀጠሉበት፡፡ ለመረጃ ትክክለኝነት እና ለዘገባ ሐቀኝነት ከመጨነቅ ይልቅ እገሌ የተባለውን ባለሥልጣን እንዳላስከፋ በምን መንገድ ላቅረበው በሚል ጉዳይ የሚጨነቁ ናቸው፡፡ አዳዲሶቹም በዚሁ ገፉበት፡፡

ቁጥራቸው እየጨመረ ቢመጣም የሚዲያን ሚና እና የጋዜጠኝነት አሠራርን እያሳደጉ ከመጓዝ ይልቅ ወደኋላ የሚጎትት እና የሚያቀጭጭ አካሔድን መርጠው እየተንከላወሱ ነው፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ሥሕተታቸውን እያረሙና እየተሻሻሉ ከመሥራት ይልቅም በቡድን ተከፋፍለው የመቆራቆሻ መሣሪያ ሆነዋል፡፡ ይህም የሚዲያውን ዕድገት ወደትናንት ከመጎተቱም በላይ ሲጀመር ከነበረበት ደረጃው ዝቅ አድርጎ ወደመድፈቅ እያንደረደራቸው ነው፡፡

የፖለቲከኞች ቁርቁስ እየሰፋ ሲመጣ ሚዲያዎቹም - በተለይም ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ግብር በሚመደብላቸው ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት ሚዲያዎችም ለተቆራቋሾቹ ወግነው በመቆም በእሳት ላይ ቤንዚን እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉበት መንገድም ከእስከዛሬው አመጣጣቸው ሁሉ እየከፋና እየወረደ መጥቷል፡፡ እስከዛሬ በነበራቸው ጉዞ እውነትን በመካድ የአንድ ወገን መረጃን ማቅረብ የነበረ ሲሆን ዛሬ ላይ ግን አንዱ የሚዲያ ተቋም የዘገበውን ቆራርጦ ያልተባለን ሐሳብ እንደተነገረ አድርጎ ማቅረብ ላይ ደርሷል፡፡ የመረጃ ሽቀባው ከእርስ በርስ መረጃዎቻቸው ዓልፎ የሌላ ሀገር ሚዲያ ዘገባን መሸቀብ ላይ ደርሷል፡፡ ይህም አንድ ወይም ሁለት የሚዲያ ተቋማት ብቻ የሚገለጹበትና እና የሚወነጀሉበት ጥፋት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የሚዲያ ተቋማት የአብዛኞቹ መገለጫ ነው፡

ይህ ሁሉ ሲታይ የኢትዮጵያ ሚዲያ እና የጋዜጠኝነት አሠራር ወደፊት ከመገሥገሥ ይልቅ ወደኋላ መንሠራተትን መሥፈርት አድርጎ የሚሠራ አስመስሎታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ እና እንደሚሠሩ እየታየም በቁጥር መበርከታቸውን እና የሚፈልገውን ሐሳብ ሲያንጸርቁለት እያየ የኢትዮጵያ ሚዲያ እድገት እያሳየ እንደሆነ የሚገልጽ እና የሚሟገት ሰውም (“ምሁር”) ቁጥሩ በርከት ያለ ነው፡፡ ይህንንም እንደስኬት ወስደውት እንደድጥ በፍጥነት ወደኋላ እያንሸራተታቸው ነው፡፡

መቼ ይሆን ይህ አሠራራቸው የሚቀየረው? መቼ ይሆን ቁልቁለት ለመውረድ ከመንደርደር ይልቅ ቀበት ለመውጣት መዳህ የሚጀምሩት?


Friday, February 14, 2020

የተስፋ ሰንሰለት



የመሸ ቢመስልህ የገባ ብርሃን የወጣ ጨለማ፣
ተስፋህ ተመናምኖ ብርክ ቢሆን ጭንቀትህ ቢሰማ፣
ኑሮህ ቢያስጎነብስ የእንብርክክ ቢያስጊዝም ግስም እያረገፈ፣
ተረት ቢያስተርትህ “ተንጋለው ቢተፉ…” ቢያሰኝህ ይህስ ቀን ባለፈ፣
ከድጡ ለማምለት እያውተረተረ መልሶ እየጣለህ ቢከትህ ከማጡ፣
እጅ አትስጠው ለእሱ የማይቀር ነው እና ነገ መለወጡ፣
በአለበሰህ ጭቃ ለራሱም በተራው ገብቶ መላቆጡ፣
ሕጉ በመኾኑ የተፈጥሮ ዑደት፣ ቢዘገይም ለውጡ፣
ድል መንሳት አይቀርም በሕወት ጉዞ ላይ ተስፋ ካልቆረጡ፡፡

እናልህ ወንድሜ፣
በዛሬ ላይ ትናንት ጠል እንዳይጥልበት፣
ደይኖ እንዳይይዘው ተክቶት ነግሦበት፣
ነገን አጠንዝሎ አክስሎት እንዳያልፍ፣
በእውቀትህ ከመራኸው ዛሬ ሳይዛነፍ፣
በእናት ማባበያ ልጅን መደለያ በእነእሰጥሃለሁ ኋላ “ጉዳጉዶ”፣
ካልተደለለ ሆድ ሚዛንን አስቶ በጥቅም ለውጦ ኅሊናን አስክዶ፣
የማታ የማታ ማሸነፍ አይቀርም ማየት ጠላት ወድቆ፣
ከቁዘማህ መውጣት በመንሰቅሰቅ ፋንታ መገኘት ፈንድቆ፡፡

ስለዚህ ወንድም ሆይ፡-
ሳንካ የሆነብህ መንገድ እየዘጋ፣ ግድግዳው ይወድቃል ተንኮታኩቶ ደቅቆ፣
መንገድህ ይጠራል ያንተ ጥረት ውጤት ከብሮ ሊታይበት ሊቆምበት ደምቆ፣
ጨለማው ይሸሻል በወጋገን ጨረር ጎኑ እየተወጋ ዛል ጥንዝል ብሎ፣
ተስፋህ እሸት ኾኖ ጎመራል የበለጠ ደምቆ የነገን ድል አዝሎ፣
እናማ፣
ዛሩህን ከያዝኸው ተጠንቅቀህለት አክብረኸው ከኖርህ የሕይወትን ሥራ፣
ነገህ ይክስሃል ወይን ይሆንልሃል የሕይወት ምሰሶ ጣፋጭ የሚያፈራ፡፡


Tuesday, December 24, 2019

ቃሌን አጥፌያለሁ!

ውዴ ሆይ!

ቃል የገባሁትን ያኔ እንድንጋባ፣
ተሳስስበን ተሳስረን ቤት እንድንገነባ፣
የገባነውን ውል አጅቦን መሃላ፣
ትቼው ረስቼው ተካሁት በሌላ፤

ውድዬ ውዲቷ!

ለምን ሆነ ካልሽም ልብሽ ከታመመ ከገባሽ ትካዜ፣
ጥያቄ ከሆንሽ የቃሌ መታጠፍ ውሉን መሰረዜ፣
የኔ ማር!
የኔም ጥያቄ ነው ያንች የሆነው ሁሉ፣
የገመድ ቋጠሮ የተበተበ የማይገኝ ውሉ፣
መስቀለኛ መንገድ መሃሉ ላይ ጥሎ ድንግርግር አድራጊ፣
ሆኖብኛል እና ከግራ ወደቀኝ የሚያመላልሰኝ እንደዘሃ ዘጊ፣
በዋገምት የማይሽር ቁርባ ሠርቶብኝ ሕማምን ስቦብኝ ከነጥላ ወጊ፣
ነቀርሳ ሆኖብኝ ጣር ቢጠናብኝ እንጂ፣ ሌላ አልተካሁብሽም ፈጽመሽ አትስጊ፤

የኔ ውድ፣ ዓለሜ!

ዓለምን የሞላት ግሳንግሱ ሁሉ፣
አልጨበጥ ብሎ ቢጠፋብኝ ውሉ፣
ስለጋብቻችን ባስብ ባሰላስል ምን ብመታ መላ፣
በዛሬ አሻግሬ እያየሁ ሳወጣ ሳወርደው የነገን ሳሰላ፣
ነገ የሚያመጣው ያ ትንሹ ልጄ ያልተሟሸው ሸክላ፣
ሕማሙን ዐይቸው ተስፋዬ መንምኖ የእምነቴ ክር ላላ፤

እናልሽ የኔ ሆድ!

ላገባሽ ያልሁትን ቃሌን አጥፌያለሁ፣
ሐሳቤን ለውጬ ሌላ ሰው ሆኛለሁ፣
ጋብቻ አስጠልቶኝ ብቸኝነት ጥሞኝ ስላገኘሁ ለኔ፣
ሰመመን ውስጥ ነኝ ቀስቃሽ የማያሻኝ የሚሆን ከጎኔ፤

ስለዚህ ናፍቆቴ!

አልመጣም፣ ጋብቻችን ቀርቶ ውላችንም ፈርሷል፣
በጋራ ያቀድነው በኔ የግል ሕልም ከተተካ ከርሟል፤

ቢሆንም ግን ውዴ!

ማፍቀሬን አልክድም መወድድሽን አልረሳም፣ አይፋቅምና መቼም ቢሆን ከቶ፣
ስንቅ ስለሆነ የተመረገ ጠጅ፣ የመንፈሴ ቀለብ የጠጣሁት ጊዜ ትዝታው ተከፍቶ።

             ታመነ ቻላቸው
             14/04/2012

Wednesday, August 21, 2019

ገድለ እስከዚያው

         
"እኔ የተፈጠርኩት ሰዎችን ለማስከፋት ነው፤ ያስከፉኝን ለማስከፋት ነው፤ ፈጣሪንም ለማስከፋት ነው።" ይላሉ።  የነተበ ልብስ ለብሰው ጥንብዝ ብለው ሰክረው እየተንገዳገዱ ይራመዳሉ። ፊታቸው በማዲያት የተሸፈነ ነው። የፊታቸው ገጽታ ያሳለፉትን የጉስቁልና ዘመን ይተርካል።
"እስከዚያው ተመልከት እባላለሁ። የእያንዳንድሽን ገመና ፀሐይ ላይ አውጥቼ እንዳሰጣ ውክልና ያለኝ ብቸኛው ግለሰብ ነኝ" ይላሉ ምን ዓይነት ቀለም እንደነበራት እንኳን ለማወቅ በምታስቸግረው ኮዳቸው ከያዙት አረቄ እየተጎነጩ። አንዳንዴ የሚከተላቸው ግሪሳ አለ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ብቻቸውን መንተል መንተል ሲሉ ይታያሉ።
ወጣቶች፣ አዋቂዎችና ሽማግሌዎች ግን ይጠየፏቸዋል። ገና ድምጻቸውን "መጣ ደግሞ ይሄ ዓለም የረሳችው አምቡላም ሽማግሌ" ሲሉ ያማርራሉ። ይሄ ግን ለእስከዚያው ቁብ አይሰጣቸውም። "ያለበት ተጉላላበት"ን ይተርቱባቸዋል። "የረከሳችሁ ስለሆናችሁ፣ ያደፈ ማንነታችሁን ለመደበቅ በኔ ያደፈ ልብስ ታፌዛላችሁ። እድፋም ሁላ! ያደፈ ጭንቅላታችሁን ከቅርጭጭቱ አላቁት። ቅርጭጭታም ሁላ! ሃሃሃሃሃሃሃሃ!..." ይሉና ወንከር ወንከር እያሉትንሽ ይራመዳሉ።
ንግግራቸው ቢያሳርራቸውም ያሽካካሉ። እስኬው ሆዬ ዘውር ይሉና "ማክላላት ላህያ አመሉ ነው። የቀራችሁ መንከባለሉ ነው። ከዘዶቻችሁ የምትለዩት በሁለት እግር በመራመድ ብቻ ነው። በቀር ቁርጥ እነወሸን! ካካካካካካካካካ ....." ይሉና እርምጃቸውን ይጀምራሉ።
ደግሞ ተመልሰው በንዴት የጦዙትን ሰዎች ያሉ። እናም "እኔ የተፈጠርሁት ሰዎችን ለማስቀየም ነው። ፈጣሪንም ቢሆን!" ይላሉ። ተንደፋድፈው በጢማቸው ይደፋሉ። ትናንትም እንደዛሬው ነበሩ፤ ነገም እንደዚያው። ይሄው ነው የእስከዚያው ገድል ጉዞ።

Monday, February 11, 2019

መግባባት ይኖረን ዘንድ ምን እናድርግ? ምንስ እንሁን?

ከዐርባ አምስት (45) ዓመታት ቀደም ብሎ የጀመረው በሐገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ የጋራ አቋም መያዝን ሽሽት ዛሬ ላይ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሷል። የአንድ ሐገር ሰዎች ተብለን እንጠራ እንጅ እርስ በእርስ የምንተያየው እንደተለያዩ ሐገራት ዜጎች ነው። እንደተለያዩ ሐገራት ብቻም ሳይሆን ታሪካዊ ጠላትነት እንዳላቸው ሐገራት ዜጎች መተያየት ከጀመርን ውለን አድረናል።

ኢትዮጵያ የሚለውን ሥም በጋራ እንጠራበት እንጂ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ የምንጋራው አቋም የለንም። በአንድ ሐገር እየኖርን፣ አንድ የይለፍ ወረቀት (Pass Port) እየተጠቀምን፣ በአንድ መንግሥት ሥር እየተዳደርን፣ ወዘተ ... የጋራችን የምንለው እና የምንስማማበት ጉዳይ ግን የለንም። 

ይኸንን ከላይ ያነሳሁትን ነጥብ የሚያስረግጡ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። በርካታ የጥቁር ሕዝብ ሐገራትና ሕዝባቸው የነጻነት ፋና ወጊ አድርገው የሚያዩትን እና እንደድላቸው አድርገው የሚቆጥሩትን የዓድዋ ድል እንኳን ልንስማማበት አልቻልንም። የእነ እከሌ ድል ነው፤ የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ ... ዓይነት የውርክብ ሐሳቦችን እየተወራወርን መናቆሪያ አድርገነዋል። ያለፈውን የኛው ታሪክ ከምንማርበት ይልቅ መበሻሸቂያ፣ መነቋቆሪያ፣ መነታረኪያ እነና የጥል ግንብ ማቆሚያ በማድረግ ላለመግባባት ስንኳትን እንውላለን።

ቋንቋን ከመግባቢያነትና ከሐሳብ መግለጫነት ነጥለን የጥልና የብጥብጥ መሣሪያ አድርገነዋል። በቋንቆቻችን ውስጥ የተከማቹ እውቀቶችን በመጋራትና በማጋራት የበሰለ ሐገራዊ አመለካከት ያለው ማኅበረሰብ ከመገንባት ይልቅ የመለያያ አጥር እየሠራንባቸው አቅጣጫው ወዳልታወቀ አድራሻ እየነጎድን ነው።  በቋንቆቻችን ውስጥ የተቀበሩ እውቀቶችን እያወጣን የጋራ የሚባል ማንነት ለመሥራት ከመጣር ይልቅ ልጆቻችን እና ታናናሾቻችን የማይግባቡበትን መንገድ ለመፍጠር የእነገሌን ቋንቋ ማወቅ የለባችሁም በማለት በእንቁላል ውስጥ እንዳለ ሽል አፍነን ለማስቀረት እንታትራለን። 

በዚህ ሁሉ ጉዟችን መግባባት የማይችል ዜጋ ለመፍጠር ተሳክቶልናል። ከተጣባን የችጋር ደከከን የሚያላቅቀን መንገድ መፈለግን ደግሞ በሚያስደምም ሁኔታ ረስተነዋል። የሰው ልጅ ያለውን በነጻነት የመሰብና የመሥራት ተፈጥሯዊ ሥጦታ በመንጠቅ ሲዋጣልን ራሳችንንም ሆነ ማኅበረሰባችንን የሚለውጥና ከድህነት አረንቋ የመምዘዣ መንገድ ለመቀየስ ግን ወገቡን እንደተመታ እባብ እየተቅመደመድን  ነው።

ለመሆኑ እንደዚህ የሆንነው ለምንድን ነው? ከዚህ የሐሳብ ድርቅና ቆፈንስ መውጣት የምንችለው እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ነው? መውጫ መንገዱን ለመፈለግስ ምን ማድረግና መሆን ይጠበቅብናል? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እያነሳን መወያየትና መሟገት አስፈላጊ ቢሆንም ረስተናቸዋል። በመሆኑም እንደግለሰብ የሚታየኝና የሚሰማኝን በዚኽች ጦማር በተከታታይ ለማቅረብ በመሞከር የድርሻየን ለመወጣት ጀምሬያለሁ። መግቢያው ይኼው። ቀጣዮቹ ክፍሎችም ይቀጥላሉ።

Tuesday, January 29, 2019

የዘንበል ዘንበል ጉዞ የት ያደርሰናል?

የኢትዮጵያን ታሪክ ስናነብም ሆነ እንደየዕድሜያችን መጠን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገዛዝ እና ለገዥዎች የነበረውንና ያለውን ዕይታና አቀባበል መረዳት ከባድ አይሆንብንም። እኔም ባነበብሁት መጠንና በሕይወት ጉዞየ በታዘብሁት መጠን ጉዳዩን የቻልሁትን ያህል ለመረዳት ጥሬያለሁ። በኔ መረዳት መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሕዝብ የአገዛዝ ሥርዓትና ገዥዎችን በተመለከተ የነበረውና ያለው አቋም "ዘንበል-ዘንበል" ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው።

ዘንበል-ዘንበል ማለት ነፋስ በሚነፍስ ወቅት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትሎ ጎንበስ ማለትን፤ እንደገናም ደግሞ ነፋሱ አቅጣጫ ቀይሮ ሲመጣ ወደተቀየረው አቅጣጫ ማጎንበስ ነው። ይህ በተፈጥሯቸው ጠንካራ ያልሆኑ የሣር ዝርያዎች ባሕሪ ነው። ሣሮች ከመነቃቀል የሚድኑት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትለው በመተኛት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብም የሣሮችን ተፈጥሯዊ ባሕሪ በመኮረጅ ከራሱ ጋር አላምዶና አዋድዶ የመጣው አገዛዝና ገዥ የያዘውን አቋም ተከትሎ እየተጓዘ የኖረና እየተጓዘም ያለ ነው። ከዚህ ባሕሪ ጋር መስማማቱንም "እንደንፋሱ አጎንብሱ" በሚል ምሳሌያዊ አነጋገር አስደግፎ የሕይወት መመሪያ እንዲሆን በማድረጉም የቀደሙትን ተከትሎ የሚመጣ አዲስ ትውልድ አገዛዝና ገዥዎችን በአዲስ መንገድ የሚያይበት መንገድ እንዳይቀርጽ ቀይዶ ይዞታል።

ዘንበል-ዘንበሉ ከሥርዓትም በላይ ግለሰብን ተመርኩዞ የተገነባ በመሆኑም አንድ ገዥ በተለየ መንገድ ሊመለክ ምንም አልቀረው እስኪባል ድረስ ለግለሰቡ ማጎብደድን ያስተማረና እያስተማረ ያለ ባሕሪ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት እንደ እንስሳ መንጋ ከፊት የቀደመው ገዥ የቀደደውን ቦይ ተከትሎ የሚፈስስ ኢ-ምክያታዊና ኢ-ተጠየቃዊ ግብስብስ አድርጎት አልፏል፤ እያለፈም ነው።

በዚህም ምክንያት ሥርዓት ገንብቶ የሚመጡ ገዥዎችን ሁሉ መምራትና መዘወር የሚያስችል መንገድ መቀየስ እንዳይቻል ሆኗል። በዚህም ምክንያት ሥልጣን የጨበጠውን ገዥ ባሕሪ ተከትለን የምንተምም ደመ-ነፍሳዊ መንጋ ሆነናል። የመጣው ሁሉ የቀደደልንን ቦይ ተከትለን የምንፈስ አስተውሎት የተሳነን ጥርቅሞች ሆነናል። የተለየ ዕይታ ያላቸውን የምንደቁስ፣ አንስተን እያፈረጥን ከመሬት የምንሰፋ ባለትንፋሽ ግዑዞችም ሆነናል።

የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን ድንብርብር እና በፍርሃት ቆፈን የተሸበብን፣ ከሥርዓት ግንባታ ይልቅ ግለሰባዊ ማንነት ላይ የምንንጠለጠል የጅምላ አስተሳሰብ ተጠቂ አድርጎናል። ሆኖም ግን ቀጥለንበታል። ዛሬም ከተቀደደልን ቦይ ባሻገር የማናይ አቅመ-ቢስ መንታሎች አድርጎናል። ራሳችንን በራሳችን የምናፍን ገራሚ ፍጡሮች አድርጎናል።

ሆኖም ዘንበል-ዘንበላችንን ለማቆም አልቻልንም፤ ወይም ለማቆም ፍላጎቱም ሆነ ፈቃዱ የለንም። ቀጥለንበታል። የት እንደሚያደርሰን ግን አናስብም። ግን ለመሆኑ ይህ የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን የት ያደርሰናል?

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡