Tuesday, January 29, 2019

የዘንበል ዘንበል ጉዞ የት ያደርሰናል?

የኢትዮጵያን ታሪክ ስናነብም ሆነ እንደየዕድሜያችን መጠን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገዛዝ እና ለገዥዎች የነበረውንና ያለውን ዕይታና አቀባበል መረዳት ከባድ አይሆንብንም። እኔም ባነበብሁት መጠንና በሕይወት ጉዞየ በታዘብሁት መጠን ጉዳዩን የቻልሁትን ያህል ለመረዳት ጥሬያለሁ። በኔ መረዳት መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሕዝብ የአገዛዝ ሥርዓትና ገዥዎችን በተመለከተ የነበረውና ያለው አቋም "ዘንበል-ዘንበል" ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው።

ዘንበል-ዘንበል ማለት ነፋስ በሚነፍስ ወቅት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትሎ ጎንበስ ማለትን፤ እንደገናም ደግሞ ነፋሱ አቅጣጫ ቀይሮ ሲመጣ ወደተቀየረው አቅጣጫ ማጎንበስ ነው። ይህ በተፈጥሯቸው ጠንካራ ያልሆኑ የሣር ዝርያዎች ባሕሪ ነው። ሣሮች ከመነቃቀል የሚድኑት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትለው በመተኛት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብም የሣሮችን ተፈጥሯዊ ባሕሪ በመኮረጅ ከራሱ ጋር አላምዶና አዋድዶ የመጣው አገዛዝና ገዥ የያዘውን አቋም ተከትሎ እየተጓዘ የኖረና እየተጓዘም ያለ ነው። ከዚህ ባሕሪ ጋር መስማማቱንም "እንደንፋሱ አጎንብሱ" በሚል ምሳሌያዊ አነጋገር አስደግፎ የሕይወት መመሪያ እንዲሆን በማድረጉም የቀደሙትን ተከትሎ የሚመጣ አዲስ ትውልድ አገዛዝና ገዥዎችን በአዲስ መንገድ የሚያይበት መንገድ እንዳይቀርጽ ቀይዶ ይዞታል።

ዘንበል-ዘንበሉ ከሥርዓትም በላይ ግለሰብን ተመርኩዞ የተገነባ በመሆኑም አንድ ገዥ በተለየ መንገድ ሊመለክ ምንም አልቀረው እስኪባል ድረስ ለግለሰቡ ማጎብደድን ያስተማረና እያስተማረ ያለ ባሕሪ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት እንደ እንስሳ መንጋ ከፊት የቀደመው ገዥ የቀደደውን ቦይ ተከትሎ የሚፈስስ ኢ-ምክያታዊና ኢ-ተጠየቃዊ ግብስብስ አድርጎት አልፏል፤ እያለፈም ነው።

በዚህም ምክንያት ሥርዓት ገንብቶ የሚመጡ ገዥዎችን ሁሉ መምራትና መዘወር የሚያስችል መንገድ መቀየስ እንዳይቻል ሆኗል። በዚህም ምክንያት ሥልጣን የጨበጠውን ገዥ ባሕሪ ተከትለን የምንተምም ደመ-ነፍሳዊ መንጋ ሆነናል። የመጣው ሁሉ የቀደደልንን ቦይ ተከትለን የምንፈስ አስተውሎት የተሳነን ጥርቅሞች ሆነናል። የተለየ ዕይታ ያላቸውን የምንደቁስ፣ አንስተን እያፈረጥን ከመሬት የምንሰፋ ባለትንፋሽ ግዑዞችም ሆነናል።

የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን ድንብርብር እና በፍርሃት ቆፈን የተሸበብን፣ ከሥርዓት ግንባታ ይልቅ ግለሰባዊ ማንነት ላይ የምንንጠለጠል የጅምላ አስተሳሰብ ተጠቂ አድርጎናል። ሆኖም ግን ቀጥለንበታል። ዛሬም ከተቀደደልን ቦይ ባሻገር የማናይ አቅመ-ቢስ መንታሎች አድርጎናል። ራሳችንን በራሳችን የምናፍን ገራሚ ፍጡሮች አድርጎናል።

ሆኖም ዘንበል-ዘንበላችንን ለማቆም አልቻልንም፤ ወይም ለማቆም ፍላጎቱም ሆነ ፈቃዱ የለንም። ቀጥለንበታል። የት እንደሚያደርሰን ግን አናስብም። ግን ለመሆኑ ይህ የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን የት ያደርሰናል?

No comments:

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡