የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የጉዞውን መነሻ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ብቅ ባሉት ጋዜጣዎች ጀምሮ በዓይነት እና በቁጥር እየሰፋ ዛሬ ላይ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጋዜጣ ምዕት ዓመት የሞላው ሲሆን የመጀመሪያው ሬዲዮ ጥር 23፣ 1927 ዓ.ም. ሥርጭቱን ከጀመረ 85 ዓመታትን አልፏል፤ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ጣሚያም ሥርጭቱን በ1957 ዓ.ም ከጀመረ 55 ዓመታትን ተጉዟል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ሚዲያ ዛሬ ላይ የተሳካላቸው እና ተጠቃሽ ሚዲያዎች ካሏቸው በርካታ ሀገራት ቀድሞ የተጀመረ መሆኑን ያሳያል፡፡
ዕድሜው
የመርዘሙን ያህል ግን ሚዲያው እና ጋዜጠኝነቱ እያደገ ከመምጣት ይልቅ ወደ መጣበት አዙሮ እያየ የኋሊት ጉዞን የመረጠ እንዲመስል
አድርጎታል፡፡ በቅርብ ዓመታት በርከት ያሉ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም የሕትመት ሚዲያዎች ተመሥርተውና ፈቃድ ተሰጥቷቸው
ሥራ ቢጀመሩም የሚዲያውን የቀደመ አካሔድ ከማስተካከል እና ጉብጠቱን ከማረቅ ይልቅ ከጉብጠቱ ጋር ተስማምተው መኖርን የመረጡ መሆናቸውን
ማንም የሚዲያዎቹ ተካታታይ ይታዘባል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት የአንድ ወገን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎች ሆነው መጡ፣ ዛሬም ቀጠሉበት፡፡
ለመረጃ ትክክለኝነት እና ለዘገባ ሐቀኝነት ከመጨነቅ ይልቅ እገሌ የተባለውን ባለሥልጣን እንዳላስከፋ በምን መንገድ ላቅረበው በሚል
ጉዳይ የሚጨነቁ ናቸው፡፡ አዳዲሶቹም በዚሁ ገፉበት፡፡
ቁጥራቸው
እየጨመረ ቢመጣም የሚዲያን ሚና እና የጋዜጠኝነት አሠራርን እያሳደጉ ከመጓዝ ይልቅ ወደኋላ የሚጎትት እና የሚያቀጭጭ አካሔድን መርጠው
እየተንከላወሱ ነው፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ሥሕተታቸውን እያረሙና እየተሻሻሉ ከመሥራት ይልቅም በቡድን ተከፋፍለው የመቆራቆሻ መሣሪያ ሆነዋል፡፡
ይህም የሚዲያውን ዕድገት ወደትናንት ከመጎተቱም በላይ ሲጀመር ከነበረበት ደረጃው ዝቅ አድርጎ ወደመድፈቅ እያንደረደራቸው ነው፡፡
የፖለቲከኞች
ቁርቁስ እየሰፋ ሲመጣ ሚዲያዎቹም - በተለይም ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ግብር በሚመደብላቸው ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት ሚዲያዎችም ለተቆራቋሾቹ
ወግነው በመቆም በእሳት ላይ ቤንዚን እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉበት መንገድም ከእስከዛሬው አመጣጣቸው ሁሉ እየከፋና
እየወረደ መጥቷል፡፡ እስከዛሬ በነበራቸው ጉዞ እውነትን በመካድ የአንድ ወገን መረጃን ማቅረብ የነበረ ሲሆን ዛሬ ላይ ግን አንዱ
የሚዲያ ተቋም የዘገበውን ቆራርጦ ያልተባለን ሐሳብ እንደተነገረ አድርጎ ማቅረብ ላይ ደርሷል፡፡ የመረጃ ሽቀባው ከእርስ በርስ መረጃዎቻቸው
ዓልፎ የሌላ ሀገር ሚዲያ ዘገባን መሸቀብ ላይ ደርሷል፡፡ ይህም አንድ ወይም ሁለት የሚዲያ ተቋማት ብቻ የሚገለጹበትና እና የሚወነጀሉበት
ጥፋት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የሚዲያ ተቋማት የአብዛኞቹ መገለጫ ነው፡
ይህ ሁሉ
ሲታይ የኢትዮጵያ ሚዲያ እና የጋዜጠኝነት አሠራር ወደፊት ከመገሥገሥ ይልቅ ወደኋላ መንሠራተትን መሥፈርት አድርጎ የሚሠራ አስመስሎታል፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ እና እንደሚሠሩ እየታየም በቁጥር መበርከታቸውን እና የሚፈልገውን ሐሳብ ሲያንጸርቁለት እያየ የኢትዮጵያ
ሚዲያ እድገት እያሳየ እንደሆነ የሚገልጽ እና የሚሟገት ሰውም (“ምሁር”) ቁጥሩ በርከት ያለ ነው፡፡ ይህንንም እንደስኬት ወስደውት
እንደድጥ በፍጥነት ወደኋላ እያንሸራተታቸው ነው፡፡
መቼ ይሆን
ይህ አሠራራቸው የሚቀየረው? መቼ ይሆን ቁልቁለት ለመውረድ ከመንደርደር ይልቅ ቀበት ለመውጣት መዳህ የሚጀምሩት?
 
No comments:
Post a Comment