ያለፉት
ዐርባ አምስት (45) ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመጠላለፍና ጣት መቀሳሰር የተሞላ እንደነበርና እንደሆነ የሚያሳዩን በርካታ ማስረጃዎች
አሉ፡፡ ይህም በዛሬው ትውልድ ላይ የቀረውን ጠባሳ ሰፊ እንዲሆንና ዐዲስና የለውጥ መሠረት የሚባለው ወጣት ሃይል በከንቱ እንዲቀር
አድርጓል፣ ዛሬም እያደረገ ነው፡፡
በነዚህ
ዓመታት እንደአሸን የፈሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካቸውን መሠረት ያደረጉት በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ላይ በመሆኑና የነሱን የአሸዋ
ላይ ውትወታ ተከትለው በነፋሱ አቅጣጫ በመመራት ታሪክ ጻፍን ያሉ ግለሰቦችም ንቅዘትን ለትውልድ የሚያስተላልፉ ትርጉም አልባና የቁርሾና
የቂም ጎተራ የሆኑ ጥራዞችን አምርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሁሉም በከፋ መልኩ ይህንን የፖለቲካና የታሪክ ዕይታ በሰፊው እያቀነቀነ
የነበረው ድርጅት የመንግሥትነትን ሚና ከተቀበለ በኋላ የነበሩት ለሠላሳ ፈሪ ዓመታት መነጣልና መጠራጠር በከፍተኛ ሁኔታ ያጎነቆለባቸውና
አሽቶም የጎመራባቸው ጊዜያት ናቸው፡፡
ሁሉም
የኔ የሚለው ጎሣ ሥር ለመጠለልና ምክንያትና ተጠየቅን ጉድጓድ ምሶ ለመቅበር ሲንደፋደፍ ራሱንና መሠረታዊ ማንነቱ ሰብአዊነትን አጉብጧል፡፡
ሁሉም ነገሮች የሚመዘኑበት መንገድም ከምክንያትና ከተጠየቅ ይልቅ ከጎሣ እና ከቋንቋ ወገንተኝነት በማስተሳሰር ሆኗል፡፡ አንደአንድ
ሐገር ዜጎች ከምናስብ ይልቅ እንደበርካታ ትንንሽ ሐገሮች በምንቆጥራቸው ጎሣዎቻችን ጥላ ሥር እንድንወሸቅ ሆነናል፡፡
የራሰችንን
ዜጋ ሐገርህ አይደለም በማለት ማፈናቀል ከጀመርን በርከት ያሉ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ያለፈው 2010 ዓ.ም እና የጀመርነው
2011 ዓ.ም ግን እጅግ የከፋው (ክፋቱ ከሚፈጸሙት አሰቃቂ ግድያዎች አንጻር ብቻ ሳይሆን ከነካቸው ጎሣዎች እና ከተፈናቀሉት ዜጎች
ቁጥርም ጭምር ነው) ይመስለኛል፡፡ ይህንነ መፈናቀል የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ከመፈናቀል በኋላ የሚደረጉ የድጋፍ እንቅስቃሴዎች
እየታዩ ያለበት ዕይታና የሚሰጣቸው የፖለቲካ ወገንተኝነት ትርጉምም ነው፡፡
ሐገሩ
ወደዚህ ምስቅልቅል እንዴት ገባች ብሎ ከሚጠይቀው ይልቅ ማን ለየትኛው ተፈናቃይ ድጋፍ አደረገ የሚለውን ጉዳይ እያሳደደ ድጋፍ አድራጊውን
አካል በጎሣና የፖለቲካ ወገንተኝነት ከረጢት ውስጥ ለመክተት የሚሽቀዳደመው ወጣት ቁጥር በብዙ እጥፍ ይልቃል፡፡ አንድ ዓመት በማይሞላ
ጊዜ ውስጥ ከ2,000,000 የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው የሐገሩ ዜጎች ከኖሩበት ቀየ መፈናቀላቸውና መጎሳቆላቸው ከሚያሳዝነው ይልቅ
የትኛው ዝነኛ ሰው ኬት አካባቢ ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ አደረገ? የትኛው አክቲቪስት ከየትኛው አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጉዳይ
አራገበ? የመሳሰሉ ጥያቄዎችን እያነሳ ሲያራግብና አቧራ ሲያጨስ የሚውለው ወጣት ቁጥር የትየለሌ ሆኗል፡፡
መፈናቀልን
ማስቆም የሚቻልበትንና ተከባብሮና ተስማምቶ መኖር የሚቻልባቸው መንገዶችን ከሚፈልገው ኃይል ይልቅ እከሌ ከዚህ አካባቢ የተፈናቀሉ
ሰዎችን የረዳው እንትን ለተባለው ብሔረሰብ ቀና አመለካከት ስለሌለው ነው፤ ከእንትን አካባቢ የተፈናቀሉት ሰዎች ድጋፍ ተዥጎድጉዶላቸው
ከእንትን አካባቢ የተፈናቀሉትን ቀና ብሎ የሚያያቸው ጠፋ፤ ወዘተ የሚሉ ጉዳዮችን እያነሳ እየጣለ ጉንጭ አልፋ ሙግት ሲሟገት የሚውለው
ይበልጣል፡፡
ከኔ ቤት
ምን ክፍተት አለ? ከሌላውስ በኩል? መፍትሔውስ ምንድን ነው? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እያነሳ ችግር የሚቀርፍ ሐሳብ ከመለዋወጥ
ይልቅ ሁሉም ሰው እኔ ባየሁበት መንገድ ማየት ካልቻለ ጠላቴ ነው የሚል ፍረጃ ውስጥ ገብቶ ለመሸናነፍና ለመዋደቅ ደፋ ቀና ሲል
የሚታይበት ሆኗል፡፡
ሆኖስ
ግን፤ ሁሌም ሰው በተፈናቀለ ቁጥር እርዳታ በማሰባሰብ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል ወይ? አንድ ጊዜ እርዳታ ያሰባሰበ ቡድን ወይም እርዳታ
የለገሰ ግለሰብና ቡድንን በዚህ የነቀዘ የፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት ሰዎች በተፈናቀሉ ቁጥር እርዳታ የመስጠት ግዴታ አለበት ወይ?
እርዳታ ማድረግ ችግሩን መስቆም ይችላል ወይ? የፖለቲካ ሥርዓቱ በዚህ መንገድ ከቀጠለ የሚፈናቀለው ሰው ከማይፈናቀለው የሚበልጥበት
ጊዜስ ሊመጣ አይችልም ወይ? ያለበት አካባቢ የሁል ጊዜ መኖሪያው እንደሆነ ተማምኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዜጋስ ምን ይህል ነው?
በመጨረሻም
ችግራችንን የበለጠ የሚያሰፉ ጉዳዮች ላይ እየተነታረክን የሚያቃቅሩን እና የበለጠ አደጋው የሚያሰፉ ጉዳዮች ላይ ተጠምደን ከምንውል
መፍትሐየ ሊያመጡልን በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሐሳብ እየተለዋወጥን የአብሮነት መንገዳችንን ብንጠርግ የተሸለ ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡