የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የመንደራችን ሙግት "ትጥቅ መፍታት እና አለመፍታት" ላይ አትኩሯል። የተለያዩ አተያዮች እና አቋሞችም እየተንጸባረቁበት ነው። ሆኖም ግን ለሙግት ማሳመኛነት እየተነሱ ካሉ አመክንዮዎች አንዱ ግን አሳማኝ ካለመሆኑም በላይ የሐሳቡን አቀንቃኞች የኢትዮጵያን ባሕል አለማወቅ ወይም እያወቁ መካዳቸውን የሚያመለክት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የመሳሪያ ባለቤት መሆን በየትኛውም የሐገራችን የገጠር ማኅበረሰብ የኩራት ምንጭና የአንድ ወንድ ሙሉ ሰውነት ማረጋገጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ከአርብቶ አደሩ እስከ አርሶ አደሩ መሳሪያ መያዝን የባሕሉ አንድ አካል አድርጎ ከመውሰዱም በላይ የመከበር ምልክቱም አድርጎ ይወስደዋል። በመሆኑም የመሳሪያ ባለቤት መሆን የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ያለ አይመስለኝም።
ስለሆነም መሳሪያን ከቤተሰቡ እንደ አንዱ ለዚያውም የብረት መዝጊያ ተብሎ እንደሚቆጠረው አድርጎ የሚወስደውን ኢትዮጵያዊ የገጠረ ነዋሪ መሳሪያህን አስረክብ ወይም ትጥቅ ፍታ ብሎ መጠየቅ የባሕሉን አንድ ጎን እርሳው የማለት ያህል የሚከብደው ነው። እንደውርደት የሚቆጠርና አስነዋሪ ተግባር እንደተፈጸመበት የሚያየውም ነው። መሳሪያ የሌለው ሌጣ መሆኑም ባሕሉ የሰጠውን የወንድነት ሚና አሳጥቶ እንደሴት የሚያስቆጥረውና በማኅበረሰቡ ዘንድም እንደፈሪና ሰነፍ የሚያስቆጥረው ነው።
ይሁን እንጅ ይህንን የማኅበረሰብ ክፍል መሳሪውን እንዲያስረክብና ትጥቅ እንዲፈታ አላደርግም የሚል ሐሳብን የተደራጀ ቡድንን ትጥቅ አላስፈታም ከሚል ሐሳብ እያነጻጸሩ ምክንያታዊ እና ትክክለኛ አስመስሎ ለማቅረብ የሚውተፈተፉ ሰዎች እየታዩ ነው። ይህም የሐገራችን ሕዝብ የገጠሩ ክፍል ማኅበረሰብ እንደመግለጫው ወስዶ የባሕሉ አካል ያደረገውን የመሳሪ ባለቤትነት ልማድ አኮስሶ የአንድ ቡድን መገለጫ ለማድረግ ከመሯሯጥ የሚተናነስ አይደለም። ለማኅበረሰብ መገለጫዎች ንቀት ከማሳየት በላይም ሽፍትነትን ማበረታታት ነው። ሰፋ ሲልም የጎሰኝነት እና የጎጠኝነት አስተሳሰብ የወለደውን እኩይ ባሕርይ እውናዊ እና ቅቡልነት ያለው አድርጎ ለማቅረብ መጣር ነው።
No comments:
Post a Comment