ብሶት
አሻግሬ እንዳላይ
ድርገት ነው ጨለማ
ዐይን የሚያስጠነቁል
ድምጽ የማያሰማ
የቅርቡን እንዳላይ ዐይኔን ይወጋኛል ጆሮዬን ደፋፍኖ
ዕውቀት ገደል ገብቶ ማስተዋል ታፍኖ ድንቁርና ገኖ፡፡
••••••••••
ሐገሬ ውስጥ የምኖር አልመስልህ እያለኝ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ፍርሃትና ስጋት የሞላበት ሆኗል፡፡ በየእለቱ ጥዋት ተነስቶ
የሚደርሰው ጸሎት ‹‹ኣባክህ ጌታየ በፌደራል ጡንቻ ከመቀጥቀጥ ጠብቀህ፣ ከደህንነት እንግልት ሰውረህ አውለህ አግባኝ›› የሆነ ይመስለኛል፡፡
እኔ እንኳን ጸሎት ሞክሬ የማላውቀው ልለው ይዳዳኛል፡፡ ሁሉም ነገር ‹‹የከንቱ ከንቱ፣ ከንቱ ነው›› የተባለው ለሐገሬ የዛሬ ሁኔታ
እንደሚስማማ ጥርጣሬ የለኝም፡፡
አገር በሙሉ ፈዝዞ ማየትን ያህል የሚያም ነገር አለ ብየ አላምንም፡፡ በየመስኩ የተበተኑ ሰዎች ሁሉ ድንቁርናን አባታቸው
ውንብድናን እናታቸው ያደረጉ በመሆናቸው ሐገር ጥቁር ለብሳለች፡፡ ዐይኗን ጥሎባታል፡፡ ሁሉን ነገሯ የሕልም ሩጫ ሆኖባታል፡፡ የሚታየው
ነገር ሁሉ ተስፋ የሚያሳጣ፣ ወደፊትም ወደኋላም ለመንቀሳቀስ መፈናፈኛ የሌለው ሆኗል፡፡
ታሪክ ያለው ሕዝብ ዛሬ እንደተወለደ ተቆጥሮ ‹‹የሕዝቦች ልደት›› የሚል ዶክመንታሪ ፊልም ሲሰራበት፣ ክብር የሚገባው
ሰብአዊ ፍጡር ከእንስሳ ያነሰ ኑሮ ሲኖርና የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ከውሻ ጋር ሲታገል ከማየት የበለጠ ምን የሚያም ነገር አለ?
ሐገር የገነባን ታላቅ ንጉሠ ነገሥት እንደ ወራሪ የሚቆጥር ወንበዴ ስልጣን ላይ ጉብ ብሎ በታላቅ ሕዝብ ላይ ሲፈነጭ፣ ደንቆሮ የወረዳና
የቀበሌ ካድሬዎች የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ፖለቲካዊ ስልጠና ሲያሰለጥኑ ሲታይ፣ ንባብ ጠላቱ የሆነ ሰው የዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ
አስተማሪ ሆኖ ሲያደነክር ሲታይ፣ የእውቀት ማቅኛና መሸመቻ የሆነ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚደንትነት የሚመራ ሰው መጽሐፍት እንዲቃጠሉ
አፉን ሞልቶ ሲናገር ሲሰማ፣ … ምን የማይቆጠቁጥ ነገር አለ፡፡
ዓለም የእንስሳት ነጻነት ያሳስበኛል የሚሉ ምሁራን ብቅ እያሉባት ባለበት ጊዜ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ መጽሐፍ እያሳተሙ
የሚቸበችቡባትን ሐገር ማየትና እሷ ውስጥም መኖር፣ አገር እመራለሁ ብሎ ዙፋን ላይ ፊጥ ያለ ሰው ተራ የሚባል ወንበዴ አንኳን ሊያወጣቸው
የሚቀፉ ቃላትን ከአፉ ሲመዝ እንደመስማት የአንድን ወጣት ልብ የሚያደማ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
በዚች በኛ ሀገር ውስጥ ከሠላሳ በላይ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩበት
መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚጠቀሙበት ሥርዓተ ትምህርት ተመሳሳይና የየተቋማቱን ሉአላዊነት የሚፈታተን ነው፡፡ ተቋማቱ በአካባቢ
ተወላጅ ይተዳደሩ የሚለው ምናልባትም ለአካባቢው ተቆርቋሪነት ይኖራቸዋል ከሚል መነሻ የመነጨ ሊሆን ቢችልም አተገባበሩ ዕውቀትን
መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ እየፈጠረ ያለው ችግር በጣም ሰፊ ነው፡፡
በአስተማሪዎቹም ሆነ በተማሪዎቹ መካከል የሚታየው ሥር የሰደደ የዘረኝነት መንፈስ ተስፋን ከተቀበረበት ጥልቅ ጉድጓድ
መንጥቆ በማውጣት እንደ ጉም ብን አድርጎ የሚያጠፋ ነው፡፡ ዘርን መሠረት አድርጎ የሚነሳ ማናቸውም ነገር የሚመራን ወደ ጨለማው
ነው፡፡ ጨለማው ደግሞ ፊታችን ላይ ታይታ የነበረችውን የብርሃን ፍንጣቂ የሚያደግዝ፡፡ ጨለማው እንዲቀርበን እየተባበሩ ካሉት ውስጥ
ከፍተኛው ሚና የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ነው፡፡
ሐገራችን ካሏት ዩኒቨርሲቲዎች በአብዛኞቹ (ሙሉ ለሙሉ ለማለት ሁሉንም የማላውቃቸው በመሆኑ ነው) አስተማሪ ሆነው ከሚሰሩት
ውስጥ በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተማሪዎቻቸውን ቋንቋቸውን መሠረት አድርገው የምዘና ውጤታቸውን ይሞላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ
ቋንቋቸውንና ዘራቸውን እንደመሣሪያ በመጠቀም ከመጡበት አካባቢ የሚመጡ ሴት ልጆችን ያባልጋሉ (ያባልጋሉ ማለት ስህተት ይመስለኛል፣
ምናልባት ይባልጋሉ ቢባል ድርጊታቸውን ይገልጸው ይሆናል)፡፡ ንፁህ ልብና እእምሮ ይዘው የመጡ ምስኪን ወጣቶችን የመመረዝ ሥራን
ይሠራሉ፡፡
የዘረኝነቱ ጉዳይ ለመግለጽ የሚከብድ ነው፡፡ ምናልባትም ራሱን በቻለ ርእስ ሰፋ ብሎ ቢብራራ በርከት ያሉ ገጾች ያሉት
ጽሑፍ ይወጣዋል፡፡ ትልቁ ጉዳይ የሞራል ልሽቀቱ ነው፡፡ አንድ መምህር ሊያስተምራቸው ፊት ለፊታቸው ከሚቆም ተማሪዎቹ ጋር አብሮ
ሲጠጣና ሲጨፍር እያደረ፤ ሰክሮ አብሮ ሲንዘላዘል እየታየ ተስፋ ያለው ሰው ሆኖ በዚች አገር መንቀሳቀስ ከተቻለ ዓለም እጅግ ድንቅ
ነገር ብላ ልትመዘግበው ይገባል፡፡
ምኑ ተነግሮ ምኑ ሊቀር እንደሚችል ማሰብ በራሱ ከባድ ነው፡፡ ማን ተወቅሶ ማን እንደሚቀር ግልጽ አይደለም፡፡ መንግሥት
ተብየው ራሳችንን ችለን መቆም እንዳንችል ደጋፊ ጡንቻዎቻችንን እያሰለለ ጅማቶቻችንን ሲመዝ የሚውል ነው፡፡ የሃይማኖት አባት ተብየዎች
አደገኛ የሚባሉ ወንበዴዎች እንኳን ሊሰሩት የማይችሉት ነውር ሲፈጽሙ እየታዩ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በራሱ የቆመበት የጠፋበት ይመስለኛል፡፡
የሚያስበው ስለሰውነት ሳይሆን ስለገንዘብ ብቻ ነው፡፡ እውቀት፣ እሴት ምናምን የሚባሉ ነገሮች አያውቅም፡፡ የሁለት አመት ልጁ ምን
ዓይነት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ማየት እንዳለበት እንኳን አያውቅም፡፡ አሰቃቂ ትዕይንቶች ያሉባቸው ፊልሞችን ህፃን ልጁን አቅፎ የሚመለከት
አባት ብዙ ነው፡፡
ምኑን አንስቶ ምኑን መተው ይቻላል? እስኪ የሚቻለን ከሆነ ብዙ ነገሮችን አብረን እናያለን፤ እናነሳለንም፡፡
No comments:
Post a Comment