Saturday, April 16, 2016

የኑሮ ቁልቁለት

ጥልቅ ነው መቀመቅ ድቅድቅ ነው ጨለማ፣
በዐይን አይታይበት ቢጮሁ አይሰማ፤
ልውጣ ቢሉ መዳህ ልግባ ቢሉ ዝቅጠት፣
ልረፍ ቢሉ ውጋት መነቃነቅ ቁስለት፤
መሄጃው መጓዣው፣ መራመጃው ሁሉ፣
መውጋት መደሰቅ ነው ትይዝትና ዓመሉ፡፡

እንዳላድግ ባጡ ይመታኛል አናቴን ይለኛል፣
ልቀመጥ እንዳልል ወንበሩ ያጥረኛል ያንጠለጥለኛል፤
መተኛት ሲያምረኝም የቤቴ ግድግዳ ዐይኑን ብልጥጥ አ‘ርጎ፣
ያስበረግገኛል እንቅልፍ እንዳላስብ ፈሪ እንድሆን አ‘ርጎ፡፡

"ከዛፉ ብጠጋ ቅጠሉ ረገፈ
ከውኃው ብጠጋ ባህሩ ነጠፈ
እንደምንም ብሎ ይህስ ቀን ባለፈ"
ቀን ነው ብየ እንዳልሄድ ፀሐይ አትታይም፣
ማታም ነው እንዳልል ጨረቃ አልወጣችም፣
ዐይኔ ነው እንዳልል ተጉረጥርጦ ያያል፣
ልቤም ነው እንዳልል ደጋግሞ ይመታል፣
የሠራ አከላቴ ሥራውን ይሠራል፣
ሕይወት በዑደቱ ዙረቱን ይዞራለረ፣
ይተኛል፣ ይነቃል ደግሞ ተደጋግሞ ይመጣል በዙሩ፣
መንፈሴ ብቻ ነው ውሉ የጠፋበት የቋጠረው ክሩ፡፡

ጋግርቱ ከበደኝ ዝምታው ተጭኖ ፀጥታው አመመኝ፣
ትንግርት ሆነብኝ፣ መደነቅ፣ መደመመም ዙሪያየን ከበበኝ፣
መመሰጥ አምሮኛል፣ ተመስጦየን ግን ወስዶታል አሞራ፣
በውስጤ መቆዘም የታጠፈ ክንፉን ዘርግቶ ሊመታ ዳንኪራ፤
ይውሰደው ግዴለም ብቆዝም አልሞትም ባልቆዝም አልጠራ፤
ላየ ሰላም ቢሆን ከውስጤ ሳልጠራ ተመስጦ ማለት ትርፉ ለኪሳራ፡፡
ጥቁር ሸማ ለባሽ ባለነጭ ክራቫት ግርማው የሚያስፈራ፣
ቢያዩት ቢያዩት አይሸሽ ክላ ቢሉት አይሄድ ቢቆጡ ቢሰዩ ትንሽ የማይፈራ፣
ስጋት የሌለበት መሙላት መጉደል አያውቅ ትርፍ የለሽ ኪሳራ፣
ደመ ነጭ ወፍ ዘራሽ መነሻ የሌለው መድረሻውን አያውቅ፣
ጥልማሞት ፋንድያ መናገር የማይችል ሲያዩት የሚያሰቅቅ፣
ሰሙ ‘ማይጠራ ስመ ብዙ ክቡር ባለ ጉልት ባለ ርስት፣

ዘሩ ‘ማይታወቅ ዘረ ብዙ ማቲ ባለብዙ ዘመድ ባለሽህ ማንነት፡፡

No comments:

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡