ስለምንም ነገር ሳስብ መንታ እየሆነብኝ ነው፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴየ በጥንድ ነገሮች እየታጀበ
ነው፡፡ ስለእድሜ አስብና አንዴ ሕፃን የሆንኩ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጨርጫሳ ሽማግሌ የሆንኩ ያህል እየተሰማኝ እቸገራለሁ፡፡ እድሜየን
በትክክል አልወቀው እንጅ ከሃያ አምስት ዓመታት ርቆ እንደማይርቅ እናቴ ደጋግማ ትነግረኛለች፡፡ ቢሆንም አብረውኝ የሚውሉ ሰዎችን
ሳይ፣ እነሱ ሁለት ፀጉር ያበቀሉ እኔ ደግሞ ጺሜ እንኳን በአግባቡ ያልበቀለ በመሆኑ ፊቴን ቁጥቋጦዎቹ የደረቁበት የበረሃ ምድር
ማስመሰሉን ስመለከት ሕፃን የሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ከሰዎቹ ተለይቼ ብቻየን በምሆን ሰዓት ደግሞ የምውልበት፣ የምሰራውና የማስበው
ከነሱ የተለየ አለመሆኑ ትዝ ይለኝና ያረጀሁ እድሜየም ሃምሳዎቹን ጨርሶ ወደ ስልሳዎቹ እየተንደረደረ ያለ ይመስለኛል፡፡ ብቻ እንደዚህም
እያሰብኩ እየኖርኩ ነው፡፡
ስለማንነቴ ሳስብ አንዳንዴ በኢትዮጵያዊነቴ ኩራት ሲሰማኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሀፍረት ይወጥረኛል፡፡ ሐገሬ
በርካታ ታሪካዊ ገድሎች ያሏት መሆኗን ሳስብ ዓለም በእጃችን ስር የገባች እስኪመስለኝ ድረስ እፍነከነክና ሳቄን ሳልጨርሰው አንድስ
እንኳን ቀደምት የሆነ የታሪክ ቅሪት በአግባቡ ክብካቤ ሲደረግለት አለማየቴ፣ ይልቁንም ቀደምቱን አፍርሶ አዳዲስ ለመትከል እሽቅድምድም
ሲደረግ ሳይ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ለማለት ይዳዳኛል (ምናዊ ነኝ ልል እንደማስብ ግን እንጃ)፡፡ በቴሌቪዥን ብቅ ብሎ ሦስት ሺህ
ዘመናት ታሪክ እንዳለኝ የነገረኝ ሰው በቀጣዩ ቀን በአካል ሳገኘው ከመቶ ዓመት የዘለለ ታሪክ የለህም ሲለኝ ላብድ ምንም አይቀረኝ፡፡
እናም ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነት የለም ለማለት እሞክርና ታሪክ ማገላበጥ ስጀምር አንተማ ንጹህ ኢትዮጵያዊ ነህ እያለ የሚጮህና
የሚሞግት መጽሐፍ አገኛለሁ፡፡ እሱን ተከትየ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብየ ወደ ውስጤ መስበክ ስጀምር ስታላዝን ትኖራታለህ እንጂ ኢትዮጵያዊነት
የምትለዋን የማንነት መገለጫ አታገኛትም የሚሉ ሌሎች ውሽልሽል መጽሐፍት እንደ አሸን ፈልተው ያድራሉ፡፡ እነርሱን መግለጥ ስጀምር
ሕመሜ ይነሳብኛል፡፡ ውስጤ ይናወጠል፡፡ ብቻ ግን እየኖርኩ ነው፡፡
ስለምማረው ትምህርት አስብና ትምህርቴን እንደጨረስኩ ወደምሰራበት ተቋም ተመልሸ መልካም ዜጎችን ለማፍራት
የሚደረገውን ጥረት አግዛለሁ ብየ ኩራት ተሰምቶኝ በብርታት ማንበብ ስጀምርና ወደ መልካም መንገድ መግባት ስጀምር አንድ እርምጃም
ሳልራመድ ፌዝን ያዘለ ሳቅ ይሰማኛል፡፡ ለካስ መልካም ዜጋ ማፍራት የሚባለው ከመንደር ወሬነት የዘለለ ወሬ አይደለ ኖሮ ሰዎች ሁሉ
በአግባቡ ለመስራት ከመጣር ይልቅ ለመስራት የሚሞክረውን የኛ ምሁር እንኳን አንተ ነህና በደጉ ጊዜ ተምረው ያለፉት ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮችም
ለውጥ ሲያመጡ አላየን፣ ይልቁንስ የሚያዋጣህን መንገድ በጊዜ ብትመርጥ ይሻልሃል ወደ ማለት ዞረናል፡፡ መቼም አስተማሪ ሆኛለሁና
ብዙ አንብቤ ማስተማር አለብኝ ብየ አስብና መጽሓፍት ለመሰብሰብ ስጣጣር አንብበውት አይደለም አይተውት ስለማያውቁት መጽሐፍ ድፍረትን
የተላበሰ ትችት እየሰነዘሩ የሚያስተምሩ ሰዎችን አያለሁ፡፡ ለማስተማር መማር ያስፈልጋል ብየ ከልቤ ተምሬ ለመለወጥ አእምሮየን ለመክፈት
ስጣጣር ሳይማሩ የሚያስተምሩ ሰዎችም መኖራቸው ውል ይለኛል፤ እናም እንባየ ይመጣል፡፡ የራሳቸውን ስራ ከሚያቀርቡ ሰዎች ይልቅም
የሌላ ሰው ሥራን የራሳቸው አስመስለው የሚያቀርቡ አፈ ጮሌዎች ሲንቆለጳጰሱ አይና ወደ ውስጤ ነስሮኝ ደምቸ ጉልበቴ ይልፈሰፈሳል፡፡
ቢሆንም መተንፈስ አላቆምኩም፡፡
ወጣትነት መልካም ነው ሁሉንም ነገር ለመሞከር ያስችላል፡፡ ጉልበት፣ እውቀትና ድፍረትን አጣምሮ ለውጥ
ለማምጣት ያስችላል የሚሉ ጽሑፎችን አንብቤ እውነትነቱን ሳልጠራጠር ዘራፍ ብየ ስነሳ፣ አርፈህ ተቀመጥ! ያነበብከው ሁሉ ያረጀ አስተሳሰብ
ያፈራው አመለካከት እንጂ ወቅታዊ ሁኔታወችን በመፈተሸ የተሰራ አይደለም፤ ቢሆንም እንኳን በኛ ሀገር ወቅታዊ እውነታ ላይ አይሰራም፡፡
ታውቃለህ እዚህች ሀገር ውስጥ ወጣትነት ማለት ተስፋህን የምታጣበት የመቀበሪያ ዘመንህ ነው፤ የምትልፈሰፈስበት እድሜም ነው የሚል
ድምጽ ተሰማኝ፡፡ ውሸታም ብየ ልከራከረው ስሞክር “ሂድ በየጉራንጉሩ ወጣቱ ምን እንደሚሰራ አይተህ ተመለስ፡፡ ከዛ በኋላ እኔን
ውሸታም ትለኛለህ፡፡ ጫት ቤት፣ ሽሻ ቤት፣ መጠጥ ቤት እና የመሳሰሉ ስፍራዎች የወጣቱ ማረፊያ መሆናቸውን አይተህ በወጣቱ ጭንቅላት
ውስጥ ያለ ትልቁ ሀሳብ ከወሲብ የሚዘል ከሆነ ከተረዳህ በኋላ እኔ ስህተት ካለብኝ ያኔ የውሸታሞች ሁሉ ውሸታም እኔ እሆናለሁ
” ብሎኝ ጸጥ አለ፡፡
እኔም ያለኝ ቦታ ሁሉ ሄድኩ፡፡ ሁሉንም አየሁ፡፡ አንዳችም ስህተት የለበትም፡፡ በወጣቱ ልፈርድ አሞክርና
የኔም ወጣትነት ትዝ ሲለኝ እተወዋለሁ፡፡ ምኑን ተስፋ አድርጎ ከዚህ ነገር ይውጣ፡፡ ሁሉም ነገር ተሟልቶለት የተደላደለ ኑሮ መኖር
የሚችለው አሁን ካለበት የአርባና የሰላሳ ዓመታት ልዩነት በኋላ ወገቡ ጎብጦ ፀጉሩ ሁለት ቀለማትን ሲያጣምር፣ ለአመለካከቱና እውቀቱ
እውቅና የሚሰጠው ኪሱ ሲያብጥና ሆዱ በመጠጥ ቅራሪ ተቆዝሮ ድርስ እርጉዝ ከመሰለ በኋላ፡፡ እናስ ምኑን ብሎ ይልፋ? እኔም እንደዛው
ለመሆን እሞክርና ያ የእርጅና ስሜቴ ትዝ ሲለኝ ዘራፍ ብየ እፎክራለሁ፡፡ ያው ዛሬም እንዳፈጠጥኩ ነኝ ማለት አይደል?
ሐገሬ ለምለሟ ጥጋብሽ የበዛ ዓይነት ስሜት የሚሰጡ ዘፈኖችን ሰምቼ አብሬ መዝፈን ስጀምር ሚሊዮን
ዐይኖች እኛም የዚህች ሐገር ልጆች ነን፣ ቢሆንም ግን ለምለምነቷ ተመችቶን ጥጋብ ሞላባት መሆኗ አጉርሶን አያውቅም፤ ይልቁንም ምቾት
ነስቶን በጠኔ ተውጠን እንድንኖር አስገደደን እንጅ ብለው አፈጠጡብኝ፡፡ በእንቅልፍ ዓለም ሆኘ ሕልም ያየሁ መስሎኝ ለሕልም አዋቂ
ነግሬ ላስፈታ ጉዞ ስጀምርም ይህ ሀሳብ አብሮኝ ይጓዛል፡፡ ተስፋየን ሟጥጦ ይዞት ይሄዳል፡፡ ሃሞቴ ፍስስ ጉልበቴ ልፍስፍስ ብሎ
ሁሉንም ነገር ለመርሳት እጣጣራለሁ፡፡ ግን አልችልም፡፡ እናም እያረርኩም ቢሆን አለሁ፡፡
ዋናው ነገር መኖሬ ነው፡፡ ገና ብዙ አያለሁ፡፡ ከፊት ለፊቴ ሁለት መንገድ ይታየኛል፡፡ ዐንዱም መንገድ
ግን ጥርት ያ አይደለም፡፡ ሁለቱም ጭጋግ የሸፈናቸው ናቸው፡፡ ገና ከወዲሁ መድረሻየን ለመተንበይ አያስችሉም፡፡ ከኋላየ ገደል ነው
ያለው፡፡ በግራና ቀኘ ደግሞ ረዥም አጥር፡፡ ብቸኛ መፍትሄው ከሁለቱ መንገዶች በአንዱ ነው፡፡ ቢሆንም የትኛውን መምረጥ እንዳለበኝ
ማወቅ ልቻልኩም፡፡ የእውር ድንብሬን እየተጓዝኩ ነው፡፡ እውነተኛውን መንገድ ሳገኘው ግን ብዙ ነገሮቼ ከጠፉ በኋላ እንደሚሆን ሳስብ
ውስጤ በእምባ ጎርፍ እየታጠበ ነው፡፡ ብቻ ትንፋሸ ሳይቋረጥ እንዲሁ ልቀጥል፡፡ … መንገዴ ሚያልቅ አይደለም!!!
No comments:
Post a Comment