Sunday, November 27, 2016

ጥሩ መጽሐፍ ማንበብ

መጻሕፍት ጥሩ ሆነው ሲቀርቡ አእምሮን ያድሳሉ፡፡ የንባብ ፍላጎትን ከተወሸቀበት ሥርቻ  መንጥቀው ያወጡታል፡፡ በተለይማ በሕይወት ልምድ ታጅበው ሲቀርቡልን፡፡
የፕሮፈሰር ሽብሩ ተድላ "ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ፤ የሕይወት ጉዞና ትዝታየ" ምንም ዓይነት የተደበተ ስሜት ውስጥ ቢሆኑ የሚኮረኩር ነው፡፡ ከታሪካዊ መረጃዎች ሐብታምነቱ እስከ ባሕል መገለጫነቱ ይህ ነው በሚባል ዋጋ ሊተመን የሚችል አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ አካባቢ ማኅበረሰብ አንዱ ከሆነው ከጎጃም ማኅበረሰብ ለማትተዋወቁ ያስተዋውቃችኋል፤ ለምትተዋወቁ ትውውቃችሁን ያደረጃል፡፡ ላደጋችሁበት ደግሞ የትዝታ መቆስቀሻ ይሆናልና አንብቡት፡፡

Wednesday, June 1, 2016

ሰው ነበር!

በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ማረሻና ድግር፣ ሞፈርና ቀንበር
ተሸክሞ ወጥቶ የሚታገል ካፈር
ማጭድና መንሹን ማርገቢያ ላይዳ
ችግሩን ሸክፎ ከትቶ በአኩፋዳ
ጋራውን የወጣ ቁልቁል የወረደ
ለግዜር እንግዳው ሲል ጠቦቱን ያረደ
የደግነት አባት፣ የልግስና እናት መሆኑን ያሳየ
ዕውቀትን ለማግኘት ማጥን የቀመሰ አሳር ችግር ያየ
የጥንካሬ ምንጭ የጀግንነት አርማ
ሐሩር ተቋቁሞ ጭንጫውን ያለማ
በቆንጥር በእሾሁ በጋሬጣው አልፎ
ድንበር የጠበቀ ለዘብ ተሰልፎ
መንገድ የጠረገ በዋሻ ቀዳዳ ማለፊያ ያመጣ
ሊወር ሊበርዘው የዘመተበትን መድረሻ ያሳጣ
አርበኛ መልምሎ ፈትኖ አንጥሮ ያወጣ
ጀግናስ ነበር ባገር የሚታወስለት ከውስጡ ያላጣ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
መልካም ሰው ያፈራ መልካም የተባለ
ምስክር ያላጣ ማንነቱን ገፍቶ ወርውሮ ያልጣለ
በፍልፈል ኵይሳ በቀበሮ ጉድጓድ ገብቶ ተወሽቆ
ጥበቡን ያሳየ ዕፁብ ሕንፃ ሠርቶ አለትን ፈቅፍቆ
መከራን ተሻግሮ ጋሩን አሳልፎ ደስታን ያነጠፈ
የቆሸሸ ለብሶ የሚበላው ቢያጣም ውስጡ ያላደፈ
ውሽንፍር ወጀቡን በጥበብ ያለፈ
ባለደማቅ አርማ ኰኰብ የለበሰ
አካሉ ያነሰ ልቡን ያነገሠ
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ሀ ብሎ ጠንቁሎ አንድ ሁለት እያለ ከድንጋይ ቆልሎ
ከካብ የዘለለ በግርማው ያማረ ትልቅ ሐውልት ላይ ሰንደቅ አሰቅሎ
በልቡ ባሕር ላይ ባንሳፈፈው ጀልባ መቅዘፍን ተምሮ
ከባሕሩም ወዲያ ከባሕሩ ወዲም ያገኘውን ሁሉ ቀምሞ መርምሮ
ሞት ብቻ ሲቀረው ሁሉን አሸንፎ
ያለፈ ሰው ነበር በሕሊናው አርፎ፡፡
       በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
      በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
በ ብሎ ደርድሮ በበገና ክሮች መንፈሱን አድሶ
ክራሩን ከርክሮ መሰንቆ ገዝግዞ አንጀቱን አርሶ
በሙዚቃው ቃና በጭፈራው ድምቀት በእልልታው ታጅቦ
ላለመደራረስ እየተማማሉ፣ ቆርጠው የነበሩን ያዋለ ሰብስቦ
ባለጎፈር ጀግና ባለለምድ ጎስቋላ
ባለበረት ንብረት ባለዕዳ መንታላ
ባለዐደራ ሆኖ ይልሰው ሳይኖረው ዐደራ ያልበላ
አጥር ተሸካሚ ሰዋሰው ደገሌ ባለሁለት ባላ
ችንካርም ምሰሶ ወጋግራ እየሆነ ጎጆ የቀለሰ
በጎረቤት ንጣት ውድቀት የቆዘመ እንባ ያለቀሰ
ቁስሉ ሳይጠግለት ሕማሙ ሳይለቀው ገመምተኛ ሳለ
የሐገሩን ጥሪ በፍርሃት በክህደት በእብለት ያልጣለ
በተፈለገበት መስክ ቀድሞ የተገኘ
ባልተማረ አንደበት ቅኔ የተቀኘ
የሆድ ነገር ብሎ ለሆድ ያልተገዛ ለሆድ ያላደረ
እንደ ልቡ ፈቃድ በሕሊናው ምሪት የጣረ የጋረ
ባለ-ስም ስም-አልባ ባለክብር ክብር ያጣ
ሐብት ሞልቶ ተርፎት ችግር ያራቆተው ቀኝ እጁ የነጣ
በነጣ ቀኝ እጁ ልሒድ ልሒድ ያለ ግራውን የቀጣ
ፍፁም ፈውስ ያገኘ አእምሮው ያረፈ ከሕሊና ቁጣ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
በፈዘዘ ሌሊት ብርሃን ፈንጥቆ ጨለመ ገፋፊ ጭላንጭል ፈንጣቂ
ከአንበሳ መንጋጋ ስጋ ያስለቀቀ ከነብር ጥፍሮች ሥር ሙዳ ተናጣቂ
እኔ ከሞትኩ ብሎ ሰርዶ ያልነቀለ
አሻራ የሚሆን ባለግርማ ሐውልት በጁ የተከለ
ሳይንስ ያላወቀ ሳይንስ ያረቀቀ
ጥበብ ያነገሠው በጥበብ የላቀ
ክክፋት ውቅያኖስ በደግነት ታንኳ ተንሳፍፎ የወጣ
ከመደንቆር ባሕር በዋና መፍጨርጨር አምልጦ የመጣ
በጨለማ ዋሻ አተምትሞ ሮጦ መንገድን የመራ ተስፈንጥሮ ወጥቶ
በእርዛት ዘመኑ ወገኑን ያልተወ ክብር ያለበሰ አጣፍቶ ድሪቶ
ችጋር ቸነፈሩን በማጎንበስ አልፎ ለጭቆና ቀንበር ያላጎነበሰ
መገዛትን ሸሽቶ መግዛት ያልመረጠ ፍርድ ያላስነከሰ
ጨለማ ሰባሪ ተወርዋሪ ኰኰብ ጅራት ያበቀለ ለእንቅልፍ ያልታደለ
መታፈን ያልገታው የጠቆረን ሰማይ በብርሃን መስመር እኩል የከፈለ
ወቀሳና ትችት ተንኰልና ሸርን ዐይቶም እንዳላየ ሰምቶም እንዳልሰማ
በደግ! ያለፋቸው መንገድ የጠረገ ያልተወላገደ ያረቀ ጠማማ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ረግረጉን አልፎ ከትልቅ ጋራ ሥር ጎጆ የቀለሰ
ያረጀ፣ የወደቀውን ቤት መልሶ ያቆመ በደሙ ያደሰ
ለቆመለት ጉዳይ አንገቱን የሰጠ ደሙን ያፈሰሰ
በጽናት ያደረ ፈተና ያልጣለው እ! ብሎ ካንጀቱ ውስጡ ያለቀሰ
መንፈሱ ያልላመ ክንዱ ያልደቀቀ
ነውር ያላሸነፈው ክብሩ ያልወደቀ
ወንድሙን እህቱን ሕዝቡን ያልሰረቀ
ወገንማ ነበር ራሱን አዋርዶ ሐገር የጠበቀ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
11/09/08
አርባ ምንጭ፣ ሲቀላ፡፡

Wednesday, April 27, 2016

ያላለቀው ሕመም

ብሶት
                                                    አሻግሬ እንዳላይ ድርገት ነው ጨለማ
                                                    ዐይን የሚያስጠነቁል ድምጽ የማያሰማ
የቅርቡን እንዳላይ ዐይኔን ይወጋኛል ጆሮዬን ደፋፍኖ
 ዕውቀት ገደል ገብቶ ማስተዋል ታፍኖ ድንቁርና ገኖ፡፡
••••••••••
ሐገሬ ውስጥ የምኖር አልመስልህ እያለኝ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ፍርሃትና ስጋት የሞላበት ሆኗል፡፡ በየእለቱ ጥዋት ተነስቶ የሚደርሰው ጸሎት ‹‹ኣባክህ ጌታየ በፌደራል ጡንቻ ከመቀጥቀጥ ጠብቀህ፣ ከደህንነት እንግልት ሰውረህ አውለህ አግባኝ›› የሆነ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንኳን ጸሎት ሞክሬ የማላውቀው ልለው ይዳዳኛል፡፡ ሁሉም ነገር ‹‹የከንቱ ከንቱ፣ ከንቱ ነው›› የተባለው ለሐገሬ የዛሬ ሁኔታ እንደሚስማማ ጥርጣሬ የለኝም፡፡
አገር በሙሉ ፈዝዞ ማየትን ያህል የሚያም ነገር አለ ብየ አላምንም፡፡ በየመስኩ የተበተኑ ሰዎች ሁሉ ድንቁርናን አባታቸው ውንብድናን እናታቸው ያደረጉ በመሆናቸው ሐገር ጥቁር ለብሳለች፡፡ ዐይኗን ጥሎባታል፡፡ ሁሉን ነገሯ የሕልም ሩጫ ሆኖባታል፡፡ የሚታየው ነገር ሁሉ ተስፋ የሚያሳጣ፣ ወደፊትም ወደኋላም ለመንቀሳቀስ መፈናፈኛ የሌለው ሆኗል፡፡
ታሪክ ያለው ሕዝብ ዛሬ እንደተወለደ ተቆጥሮ ‹‹የሕዝቦች ልደት›› የሚል ዶክመንታሪ ፊልም ሲሰራበት፣ ክብር የሚገባው ሰብአዊ ፍጡር ከእንስሳ ያነሰ ኑሮ ሲኖርና የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ከውሻ ጋር ሲታገል ከማየት የበለጠ ምን የሚያም ነገር አለ? ሐገር የገነባን ታላቅ ንጉሠ ነገሥት እንደ ወራሪ የሚቆጥር ወንበዴ ስልጣን ላይ ጉብ ብሎ በታላቅ ሕዝብ ላይ ሲፈነጭ፣ ደንቆሮ የወረዳና የቀበሌ ካድሬዎች የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ፖለቲካዊ ስልጠና ሲያሰለጥኑ ሲታይ፣ ንባብ ጠላቱ የሆነ ሰው የዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ አስተማሪ ሆኖ ሲያደነክር ሲታይ፣ የእውቀት ማቅኛና መሸመቻ የሆነ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚደንትነት የሚመራ ሰው መጽሐፍት እንዲቃጠሉ አፉን ሞልቶ ሲናገር ሲሰማ፣ … ምን የማይቆጠቁጥ ነገር አለ፡፡
ዓለም የእንስሳት ነጻነት ያሳስበኛል የሚሉ ምሁራን ብቅ እያሉባት ባለበት ጊዜ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ መጽሐፍ እያሳተሙ የሚቸበችቡባትን ሐገር ማየትና እሷ ውስጥም መኖር፣ አገር እመራለሁ ብሎ ዙፋን ላይ ፊጥ ያለ ሰው ተራ የሚባል ወንበዴ አንኳን ሊያወጣቸው የሚቀፉ ቃላትን ከአፉ ሲመዝ እንደመስማት የአንድን ወጣት ልብ የሚያደማ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
በዚች በኛ ሀገር ውስጥ ከሠላሳ በላይ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚጠቀሙበት ሥርዓተ ትምህርት ተመሳሳይና የየተቋማቱን ሉአላዊነት የሚፈታተን ነው፡፡ ተቋማቱ በአካባቢ ተወላጅ ይተዳደሩ የሚለው ምናልባትም ለአካባቢው ተቆርቋሪነት ይኖራቸዋል ከሚል መነሻ የመነጨ ሊሆን ቢችልም አተገባበሩ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ እየፈጠረ ያለው ችግር በጣም ሰፊ ነው፡፡
በአስተማሪዎቹም ሆነ በተማሪዎቹ መካከል የሚታየው ሥር የሰደደ የዘረኝነት መንፈስ ተስፋን ከተቀበረበት ጥልቅ ጉድጓድ መንጥቆ በማውጣት እንደ ጉም ብን አድርጎ የሚያጠፋ ነው፡፡ ዘርን መሠረት አድርጎ የሚነሳ ማናቸውም ነገር የሚመራን ወደ ጨለማው ነው፡፡ ጨለማው ደግሞ ፊታችን ላይ ታይታ የነበረችውን የብርሃን ፍንጣቂ የሚያደግዝ፡፡ ጨለማው እንዲቀርበን እየተባበሩ ካሉት ውስጥ ከፍተኛው ሚና የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ነው፡፡
ሐገራችን ካሏት ዩኒቨርሲቲዎች በአብዛኞቹ (ሙሉ ለሙሉ ለማለት ሁሉንም የማላውቃቸው በመሆኑ ነው) አስተማሪ ሆነው ከሚሰሩት ውስጥ በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተማሪዎቻቸውን ቋንቋቸውን መሠረት አድርገው የምዘና ውጤታቸውን ይሞላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ቋንቋቸውንና ዘራቸውን እንደመሣሪያ በመጠቀም ከመጡበት አካባቢ የሚመጡ ሴት ልጆችን ያባልጋሉ (ያባልጋሉ ማለት ስህተት ይመስለኛል፣ ምናልባት ይባልጋሉ ቢባል ድርጊታቸውን ይገልጸው ይሆናል)፡፡ ንፁህ ልብና እእምሮ ይዘው የመጡ ምስኪን ወጣቶችን የመመረዝ ሥራን ይሠራሉ፡፡
የዘረኝነቱ ጉዳይ ለመግለጽ የሚከብድ ነው፡፡ ምናልባትም ራሱን በቻለ ርእስ ሰፋ ብሎ ቢብራራ በርከት ያሉ ገጾች ያሉት ጽሑፍ ይወጣዋል፡፡ ትልቁ ጉዳይ የሞራል ልሽቀቱ ነው፡፡ አንድ መምህር ሊያስተምራቸው ፊት ለፊታቸው ከሚቆም ተማሪዎቹ ጋር አብሮ ሲጠጣና ሲጨፍር እያደረ፤ ሰክሮ አብሮ ሲንዘላዘል እየታየ ተስፋ ያለው ሰው ሆኖ በዚች አገር መንቀሳቀስ ከተቻለ ዓለም እጅግ ድንቅ ነገር ብላ ልትመዘግበው ይገባል፡፡
ምኑ ተነግሮ ምኑ ሊቀር እንደሚችል ማሰብ በራሱ ከባድ ነው፡፡ ማን ተወቅሶ ማን እንደሚቀር ግልጽ አይደለም፡፡ መንግሥት ተብየው ራሳችንን ችለን መቆም እንዳንችል ደጋፊ ጡንቻዎቻችንን እያሰለለ ጅማቶቻችንን ሲመዝ የሚውል ነው፡፡ የሃይማኖት አባት ተብየዎች አደገኛ የሚባሉ ወንበዴዎች እንኳን ሊሰሩት የማይችሉት ነውር ሲፈጽሙ እየታዩ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በራሱ የቆመበት የጠፋበት ይመስለኛል፡፡ የሚያስበው ስለሰውነት ሳይሆን ስለገንዘብ ብቻ ነው፡፡ እውቀት፣ እሴት ምናምን የሚባሉ ነገሮች አያውቅም፡፡ የሁለት አመት ልጁ ምን ዓይነት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ማየት እንዳለበት እንኳን አያውቅም፡፡ አሰቃቂ ትዕይንቶች ያሉባቸው ፊልሞችን ህፃን ልጁን አቅፎ የሚመለከት አባት ብዙ ነው፡፡

ምኑን አንስቶ ምኑን መተው ይቻላል? እስኪ የሚቻለን ከሆነ ብዙ ነገሮችን አብረን እናያለን፤ እናነሳለንም፡፡

Saturday, April 16, 2016

ተስፋ የለሽ መንግሥት

የሆነ የአገራችን ጫፍ ላይ ከጎረቤት አገር የመጡ ታጣቂዎች ጥቃት ሲያደርሱ ኃላፊነት ወስዶ ተመጣጣኝ እርምጃ የሚወስደው አሊያም ከታጣቂዎቹ አገር መንግሥት ጋር በመደራደር እርምጃ የማስወሰድ እና ለተበዳዮችም ካሳ የማስከፈል ኃላፊኀቱ ግን የማን ነው? የፌደራሉ መንግሥት፣ የክልል መንግሥታት ወይስ የአካባቢው ጎሳ አለቆች? 140 ዜጎቹ አልቀው ወንበዴ ምናምን እያለ የሚቀባጥረው ግን መንግሥታችን ነው የሚባለው? ማንኛውም (አምባገነንነት እስካፍንጫው የወጣበትም) መንግሥት የሚገዛው ምድር ሰዎች ሲደፈሩ የደፈሯቸውን ይቀጣል፡፡ መቅጣት ካልቻለ እንኳን ዓለም አቀፍ ፍትህ የሚገኝበትን መንገድ ይፈልጋል፡፡ ዜጎቹን ራሱ ቢበድላቸውም ሌላ እንዲነካቸው ግን አይፈቅድም፡፡ የኛው ግን እንደ ዩግሌና መደብ አልባ ገዢ ሆኖ ነው መሰል ራሱ በድሎ ለሌላውም እያሳለፈ እየሰጠን ነው፡፡
በ#ጋምቤላ የደረሰው ጥቃት የጋምቤላ ብቻ ጥቃት አይደለም፡፡ 100, 000, 000 ሰዎች ናቸው የተጠቁት፡፡ የነሱ መንግሥት ተብየውም ነው የተናቀው፡፡
የተናቀ መንግሥትን ያህል የሚያሸማቅቅ ግን ምን አለ?

የኑሮ ቁልቁለት

ጥልቅ ነው መቀመቅ ድቅድቅ ነው ጨለማ፣
በዐይን አይታይበት ቢጮሁ አይሰማ፤
ልውጣ ቢሉ መዳህ ልግባ ቢሉ ዝቅጠት፣
ልረፍ ቢሉ ውጋት መነቃነቅ ቁስለት፤
መሄጃው መጓዣው፣ መራመጃው ሁሉ፣
መውጋት መደሰቅ ነው ትይዝትና ዓመሉ፡፡

እንዳላድግ ባጡ ይመታኛል አናቴን ይለኛል፣
ልቀመጥ እንዳልል ወንበሩ ያጥረኛል ያንጠለጥለኛል፤
መተኛት ሲያምረኝም የቤቴ ግድግዳ ዐይኑን ብልጥጥ አ‘ርጎ፣
ያስበረግገኛል እንቅልፍ እንዳላስብ ፈሪ እንድሆን አ‘ርጎ፡፡

"ከዛፉ ብጠጋ ቅጠሉ ረገፈ
ከውኃው ብጠጋ ባህሩ ነጠፈ
እንደምንም ብሎ ይህስ ቀን ባለፈ"
ቀን ነው ብየ እንዳልሄድ ፀሐይ አትታይም፣
ማታም ነው እንዳልል ጨረቃ አልወጣችም፣
ዐይኔ ነው እንዳልል ተጉረጥርጦ ያያል፣
ልቤም ነው እንዳልል ደጋግሞ ይመታል፣
የሠራ አከላቴ ሥራውን ይሠራል፣
ሕይወት በዑደቱ ዙረቱን ይዞራለረ፣
ይተኛል፣ ይነቃል ደግሞ ተደጋግሞ ይመጣል በዙሩ፣
መንፈሴ ብቻ ነው ውሉ የጠፋበት የቋጠረው ክሩ፡፡

ጋግርቱ ከበደኝ ዝምታው ተጭኖ ፀጥታው አመመኝ፣
ትንግርት ሆነብኝ፣ መደነቅ፣ መደመመም ዙሪያየን ከበበኝ፣
መመሰጥ አምሮኛል፣ ተመስጦየን ግን ወስዶታል አሞራ፣
በውስጤ መቆዘም የታጠፈ ክንፉን ዘርግቶ ሊመታ ዳንኪራ፤
ይውሰደው ግዴለም ብቆዝም አልሞትም ባልቆዝም አልጠራ፤
ላየ ሰላም ቢሆን ከውስጤ ሳልጠራ ተመስጦ ማለት ትርፉ ለኪሳራ፡፡
ጥቁር ሸማ ለባሽ ባለነጭ ክራቫት ግርማው የሚያስፈራ፣
ቢያዩት ቢያዩት አይሸሽ ክላ ቢሉት አይሄድ ቢቆጡ ቢሰዩ ትንሽ የማይፈራ፣
ስጋት የሌለበት መሙላት መጉደል አያውቅ ትርፍ የለሽ ኪሳራ፣
ደመ ነጭ ወፍ ዘራሽ መነሻ የሌለው መድረሻውን አያውቅ፣
ጥልማሞት ፋንድያ መናገር የማይችል ሲያዩት የሚያሰቅቅ፣
ሰሙ ‘ማይጠራ ስመ ብዙ ክቡር ባለ ጉልት ባለ ርስት፣

ዘሩ ‘ማይታወቅ ዘረ ብዙ ማቲ ባለብዙ ዘመድ ባለሽህ ማንነት፡፡

Thursday, April 14, 2016

ያላለቀው ...

ስለምንም ነገር ሳስብ መንታ እየሆነብኝ ነው፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴየ በጥንድ ነገሮች እየታጀበ ነው፡፡ ስለእድሜ አስብና አንዴ ሕፃን የሆንኩ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጨርጫሳ ሽማግሌ የሆንኩ ያህል እየተሰማኝ እቸገራለሁ፡፡ እድሜየን በትክክል አልወቀው እንጅ ከሃያ አምስት ዓመታት ርቆ እንደማይርቅ እናቴ ደጋግማ ትነግረኛለች፡፡ ቢሆንም አብረውኝ የሚውሉ ሰዎችን ሳይ፣ እነሱ ሁለት ፀጉር ያበቀሉ እኔ ደግሞ ጺሜ እንኳን በአግባቡ ያልበቀለ በመሆኑ ፊቴን ቁጥቋጦዎቹ የደረቁበት የበረሃ ምድር ማስመሰሉን ስመለከት ሕፃን የሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ከሰዎቹ ተለይቼ ብቻየን በምሆን ሰዓት ደግሞ የምውልበት፣ የምሰራውና የማስበው ከነሱ የተለየ አለመሆኑ ትዝ ይለኝና ያረጀሁ እድሜየም ሃምሳዎቹን ጨርሶ ወደ ስልሳዎቹ እየተንደረደረ ያለ ይመስለኛል፡፡ ብቻ እንደዚህም እያሰብኩ እየኖርኩ ነው፡፡
ስለማንነቴ ሳስብ አንዳንዴ በኢትዮጵያዊነቴ ኩራት ሲሰማኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሀፍረት ይወጥረኛል፡፡ ሐገሬ በርካታ ታሪካዊ ገድሎች ያሏት መሆኗን ሳስብ ዓለም በእጃችን ስር የገባች እስኪመስለኝ ድረስ እፍነከነክና ሳቄን ሳልጨርሰው አንድስ እንኳን ቀደምት የሆነ የታሪክ ቅሪት በአግባቡ ክብካቤ ሲደረግለት አለማየቴ፣ ይልቁንም ቀደምቱን አፍርሶ አዳዲስ ለመትከል እሽቅድምድም ሲደረግ ሳይ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ለማለት ይዳዳኛል (ምናዊ ነኝ ልል እንደማስብ ግን እንጃ)፡፡ በቴሌቪዥን ብቅ ብሎ ሦስት ሺህ ዘመናት ታሪክ እንዳለኝ የነገረኝ ሰው በቀጣዩ ቀን በአካል ሳገኘው ከመቶ ዓመት የዘለለ ታሪክ የለህም ሲለኝ ላብድ ምንም አይቀረኝ፡፡ እናም ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነት የለም ለማለት እሞክርና ታሪክ ማገላበጥ ስጀምር አንተማ ንጹህ ኢትዮጵያዊ ነህ እያለ የሚጮህና የሚሞግት መጽሐፍ አገኛለሁ፡፡ እሱን ተከትየ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብየ ወደ ውስጤ መስበክ ስጀምር ስታላዝን ትኖራታለህ እንጂ ኢትዮጵያዊነት የምትለዋን የማንነት መገለጫ አታገኛትም የሚሉ ሌሎች ውሽልሽል መጽሐፍት እንደ አሸን ፈልተው ያድራሉ፡፡ እነርሱን መግለጥ ስጀምር ሕመሜ ይነሳብኛል፡፡ ውስጤ ይናወጠል፡፡ ብቻ ግን እየኖርኩ ነው፡፡
ስለምማረው ትምህርት አስብና ትምህርቴን እንደጨረስኩ ወደምሰራበት ተቋም ተመልሸ መልካም ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት አግዛለሁ ብየ ኩራት ተሰምቶኝ በብርታት ማንበብ ስጀምርና ወደ መልካም መንገድ መግባት ስጀምር አንድ እርምጃም ሳልራመድ ፌዝን ያዘለ ሳቅ ይሰማኛል፡፡ ለካስ መልካም ዜጋ ማፍራት የሚባለው ከመንደር ወሬነት የዘለለ ወሬ አይደለ ኖሮ ሰዎች ሁሉ በአግባቡ ለመስራት ከመጣር ይልቅ ለመስራት የሚሞክረውን የኛ ምሁር እንኳን አንተ ነህና በደጉ ጊዜ ተምረው ያለፉት ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮችም ለውጥ ሲያመጡ አላየን፣ ይልቁንስ የሚያዋጣህን መንገድ በጊዜ ብትመርጥ ይሻልሃል ወደ ማለት ዞረናል፡፡ መቼም አስተማሪ ሆኛለሁና ብዙ አንብቤ ማስተማር አለብኝ ብየ አስብና መጽሓፍት ለመሰብሰብ ስጣጣር አንብበውት አይደለም አይተውት ስለማያውቁት መጽሐፍ ድፍረትን የተላበሰ ትችት እየሰነዘሩ የሚያስተምሩ ሰዎችን አያለሁ፡፡ ለማስተማር መማር ያስፈልጋል ብየ ከልቤ ተምሬ ለመለወጥ አእምሮየን ለመክፈት ስጣጣር ሳይማሩ የሚያስተምሩ ሰዎችም መኖራቸው ውል ይለኛል፤ እናም እንባየ ይመጣል፡፡ የራሳቸውን ስራ ከሚያቀርቡ ሰዎች ይልቅም የሌላ ሰው ሥራን የራሳቸው አስመስለው የሚያቀርቡ አፈ ጮሌዎች ሲንቆለጳጰሱ አይና ወደ ውስጤ ነስሮኝ ደምቸ ጉልበቴ ይልፈሰፈሳል፡፡ ቢሆንም መተንፈስ አላቆምኩም፡፡
ወጣትነት መልካም ነው ሁሉንም ነገር ለመሞከር ያስችላል፡፡ ጉልበት፣ እውቀትና ድፍረትን አጣምሮ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል የሚሉ ጽሑፎችን አንብቤ እውነትነቱን ሳልጠራጠር ዘራፍ ብየ ስነሳ፣ አርፈህ ተቀመጥ! ያነበብከው ሁሉ ያረጀ አስተሳሰብ ያፈራው አመለካከት እንጂ ወቅታዊ ሁኔታወችን በመፈተሸ የተሰራ አይደለም፤ ቢሆንም እንኳን በኛ ሀገር ወቅታዊ እውነታ ላይ አይሰራም፡፡ ታውቃለህ እዚህች ሀገር ውስጥ ወጣትነት ማለት ተስፋህን የምታጣበት የመቀበሪያ ዘመንህ ነው፤ የምትልፈሰፈስበት እድሜም ነው የሚል ድምጽ ተሰማኝ፡፡ ውሸታም ብየ ልከራከረው ስሞክር “ሂድ በየጉራንጉሩ ወጣቱ ምን እንደሚሰራ አይተህ ተመለስ፡፡ ከዛ በኋላ እኔን ውሸታም ትለኛለህ፡፡ ጫት ቤት፣ ሽሻ ቤት፣ መጠጥ ቤት እና የመሳሰሉ ስፍራዎች የወጣቱ ማረፊያ መሆናቸውን አይተህ በወጣቱ ጭንቅላት ውስጥ ያለ ትልቁ ሀሳብ ከወሲብ የሚዘል ከሆነ ከተረዳህ በኋላ እኔ ስህተት ካለብኝ ያኔ የውሸታሞች ሁሉ ውሸታም እኔ እሆናለሁ ” ብሎኝ ጸጥ አለ፡፡
እኔም ያለኝ ቦታ ሁሉ ሄድኩ፡፡ ሁሉንም አየሁ፡፡ አንዳችም ስህተት የለበትም፡፡ በወጣቱ ልፈርድ አሞክርና የኔም ወጣትነት ትዝ ሲለኝ እተወዋለሁ፡፡ ምኑን ተስፋ አድርጎ ከዚህ ነገር ይውጣ፡፡ ሁሉም ነገር ተሟልቶለት የተደላደለ ኑሮ መኖር የሚችለው አሁን ካለበት የአርባና የሰላሳ ዓመታት ልዩነት በኋላ ወገቡ ጎብጦ ፀጉሩ ሁለት ቀለማትን ሲያጣምር፣ ለአመለካከቱና እውቀቱ እውቅና የሚሰጠው ኪሱ ሲያብጥና ሆዱ በመጠጥ ቅራሪ ተቆዝሮ ድርስ እርጉዝ ከመሰለ በኋላ፡፡ እናስ ምኑን ብሎ ይልፋ? እኔም እንደዛው ለመሆን እሞክርና ያ የእርጅና ስሜቴ ትዝ ሲለኝ ዘራፍ ብየ እፎክራለሁ፡፡ ያው ዛሬም እንዳፈጠጥኩ ነኝ ማለት አይደል?
ሐገሬ ለምለሟ ጥጋብሽ የበዛ ዓይነት ስሜት የሚሰጡ ዘፈኖችን ሰምቼ አብሬ መዝፈን ስጀምር ሚሊዮን ዐይኖች እኛም የዚህች ሐገር ልጆች ነን፣ ቢሆንም ግን ለምለምነቷ ተመችቶን ጥጋብ ሞላባት መሆኗ አጉርሶን አያውቅም፤ ይልቁንም ምቾት ነስቶን በጠኔ ተውጠን እንድንኖር አስገደደን እንጅ ብለው አፈጠጡብኝ፡፡ በእንቅልፍ ዓለም ሆኘ ሕልም ያየሁ መስሎኝ ለሕልም አዋቂ ነግሬ ላስፈታ ጉዞ ስጀምርም ይህ ሀሳብ አብሮኝ ይጓዛል፡፡ ተስፋየን ሟጥጦ ይዞት ይሄዳል፡፡ ሃሞቴ ፍስስ ጉልበቴ ልፍስፍስ ብሎ ሁሉንም ነገር ለመርሳት እጣጣራለሁ፡፡ ግን አልችልም፡፡ እናም እያረርኩም ቢሆን አለሁ፡፡
ዋናው ነገር መኖሬ ነው፡፡ ገና ብዙ አያለሁ፡፡ ከፊት ለፊቴ ሁለት መንገድ ይታየኛል፡፡ ዐንዱም መንገድ ግን ጥርት ያ አይደለም፡፡ ሁለቱም ጭጋግ የሸፈናቸው ናቸው፡፡ ገና ከወዲሁ መድረሻየን ለመተንበይ አያስችሉም፡፡ ከኋላየ ገደል ነው ያለው፡፡ በግራና ቀኘ ደግሞ ረዥም አጥር፡፡ ብቸኛ መፍትሄው ከሁለቱ መንገዶች በአንዱ ነው፡፡ ቢሆንም የትኛውን መምረጥ እንዳለበኝ ማወቅ ልቻልኩም፡፡ የእውር ድንብሬን እየተጓዝኩ ነው፡፡ እውነተኛውን መንገድ ሳገኘው ግን ብዙ ነገሮቼ ከጠፉ በኋላ እንደሚሆን ሳስብ ውስጤ በእምባ ጎርፍ እየታጠበ ነው፡፡ ብቻ ትንፋሸ ሳይቋረጥ እንዲሁ ልቀጥል፡፡ …  መንገዴ ሚያልቅ አይደለም!!! 

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡