ምናምኒት ነገር እጅህ ላይ ባይገኝ ብታጣ ብትነጣ፣
እሳት
ተለቅቆብህ ከቤት ብትሳደድ ሜዳ ብትሰጣ፣
አዝመራህም
ነድዶ ጨገሬታ ጠፍቶ ጠኔህም ቢበዛ፣
ዕድል
ፊት ብተነሳህ አሳዳጅ የሚሆን ተላትህን ብትገዛ፣
አይክፋህ ወንድሜ፣
በደል አይሰማህ መገፋት መጣልህ ፈፅሞ አያስከፋህ፤
ምክንያቱም፣
አንተ ማለት ለዓለም "ምንም ነህ ማንም ነህ"።
ወገኔ ነው ያልኸው እምነት
ጥለህበት ያደረግኸው ተስፋ፣
ቢሸሽ ቢሸሸግም ርቆ እየሔደ
ካይንህ ተተሰውሮ ከጎንህ ቢጠፋ፣
ጊዜ እየታከከ ጉልበት ቢያጎለብት
ለውድቀትህ ቢቆም አንተኑ ሊገፋ፣
ብንን ብሎ ቢሔድ ነፋስ
እንደገፋው እንደጉም ቀሎ የጣልህበት ተስፋ፣
አይክፋህ ወንድሜ፣
በደል አይሰማህ መገፋት መጣልህ ፈፅሞ አያስከፋህ፤
ምክንያቱም፣
አንተ ማለት ለዓለም "ምንም ነህ ማንም ነህ"።
የምትገብርለት
ዓመት እየጠበቅህ፣
ቆሜያለሁ
የሚልህ አንተን ልጠብቅህ፣
ካጥቂዎችህ
ቢያብር ደጋግሞ ቢክድህ፣
ዓለም ስለተወህ ዓለም ስለረሳህ፣
አይክፋህ ወንድሜ በደል አይሰማህ፣
ይልቅስ፣
ቅስምህን አበርታ
መንፈስህን አጽና፣
ቀበቶህን አጥብቅ
አንገትህንም አቅና፣
አንተን የሚታደግ
አውጪ ከፈተና፣
ከራሥህ በስተቀር
ማንም የለምና፤
አልያማ፣
ጥረህ ተጣጥረህ ታግለህ
ካላሸነፍህ ካልወጣህ አርነት፣
ዝምታህ ብርታቱ መታገስህ
ኃይል ሆኖት ጉልበት፣
ሽህ ምንተሸህ ሆኖ
ተንጋግቶ ይመጣል፣
የቅስምህ መሰበር
ውስጡን ወኔ ሞልቶት፣
ኪሱን ሊያደላድል
ሊሞላው የሱን ቤት፣
ትርፉን እያሰላ ሊሸጥ
ያንተን ሕይወት፣
ምክንያቱም፣
ራሥህ ለራሥህ መድኃኒት
ካልሆንኸው መንፈስህ በርትቶ፣
ደድረህ ካልመከትህ
ኃይልህ ተጠራቅሞ ቅስምህም ጎልብቶ፣
ዓለም አይሰማህም
ደራሽም የለህም፣
የሚገፋህ እንጂ
ደጋፊ አታገኝም፡፡