Friday, February 14, 2020

የተስፋ ሰንሰለት



የመሸ ቢመስልህ የገባ ብርሃን የወጣ ጨለማ፣
ተስፋህ ተመናምኖ ብርክ ቢሆን ጭንቀትህ ቢሰማ፣
ኑሮህ ቢያስጎነብስ የእንብርክክ ቢያስጊዝም ግስም እያረገፈ፣
ተረት ቢያስተርትህ “ተንጋለው ቢተፉ…” ቢያሰኝህ ይህስ ቀን ባለፈ፣
ከድጡ ለማምለት እያውተረተረ መልሶ እየጣለህ ቢከትህ ከማጡ፣
እጅ አትስጠው ለእሱ የማይቀር ነው እና ነገ መለወጡ፣
በአለበሰህ ጭቃ ለራሱም በተራው ገብቶ መላቆጡ፣
ሕጉ በመኾኑ የተፈጥሮ ዑደት፣ ቢዘገይም ለውጡ፣
ድል መንሳት አይቀርም በሕወት ጉዞ ላይ ተስፋ ካልቆረጡ፡፡

እናልህ ወንድሜ፣
በዛሬ ላይ ትናንት ጠል እንዳይጥልበት፣
ደይኖ እንዳይይዘው ተክቶት ነግሦበት፣
ነገን አጠንዝሎ አክስሎት እንዳያልፍ፣
በእውቀትህ ከመራኸው ዛሬ ሳይዛነፍ፣
በእናት ማባበያ ልጅን መደለያ በእነእሰጥሃለሁ ኋላ “ጉዳጉዶ”፣
ካልተደለለ ሆድ ሚዛንን አስቶ በጥቅም ለውጦ ኅሊናን አስክዶ፣
የማታ የማታ ማሸነፍ አይቀርም ማየት ጠላት ወድቆ፣
ከቁዘማህ መውጣት በመንሰቅሰቅ ፋንታ መገኘት ፈንድቆ፡፡

ስለዚህ ወንድም ሆይ፡-
ሳንካ የሆነብህ መንገድ እየዘጋ፣ ግድግዳው ይወድቃል ተንኮታኩቶ ደቅቆ፣
መንገድህ ይጠራል ያንተ ጥረት ውጤት ከብሮ ሊታይበት ሊቆምበት ደምቆ፣
ጨለማው ይሸሻል በወጋገን ጨረር ጎኑ እየተወጋ ዛል ጥንዝል ብሎ፣
ተስፋህ እሸት ኾኖ ጎመራል የበለጠ ደምቆ የነገን ድል አዝሎ፣
እናማ፣
ዛሩህን ከያዝኸው ተጠንቅቀህለት አክብረኸው ከኖርህ የሕይወትን ሥራ፣
ነገህ ይክስሃል ወይን ይሆንልሃል የሕይወት ምሰሶ ጣፋጭ የሚያፈራ፡፡


Tuesday, December 24, 2019

ቃሌን አጥፌያለሁ!

ውዴ ሆይ!

ቃል የገባሁትን ያኔ እንድንጋባ፣
ተሳስስበን ተሳስረን ቤት እንድንገነባ፣
የገባነውን ውል አጅቦን መሃላ፣
ትቼው ረስቼው ተካሁት በሌላ፤

ውድዬ ውዲቷ!

ለምን ሆነ ካልሽም ልብሽ ከታመመ ከገባሽ ትካዜ፣
ጥያቄ ከሆንሽ የቃሌ መታጠፍ ውሉን መሰረዜ፣
የኔ ማር!
የኔም ጥያቄ ነው ያንች የሆነው ሁሉ፣
የገመድ ቋጠሮ የተበተበ የማይገኝ ውሉ፣
መስቀለኛ መንገድ መሃሉ ላይ ጥሎ ድንግርግር አድራጊ፣
ሆኖብኛል እና ከግራ ወደቀኝ የሚያመላልሰኝ እንደዘሃ ዘጊ፣
በዋገምት የማይሽር ቁርባ ሠርቶብኝ ሕማምን ስቦብኝ ከነጥላ ወጊ፣
ነቀርሳ ሆኖብኝ ጣር ቢጠናብኝ እንጂ፣ ሌላ አልተካሁብሽም ፈጽመሽ አትስጊ፤

የኔ ውድ፣ ዓለሜ!

ዓለምን የሞላት ግሳንግሱ ሁሉ፣
አልጨበጥ ብሎ ቢጠፋብኝ ውሉ፣
ስለጋብቻችን ባስብ ባሰላስል ምን ብመታ መላ፣
በዛሬ አሻግሬ እያየሁ ሳወጣ ሳወርደው የነገን ሳሰላ፣
ነገ የሚያመጣው ያ ትንሹ ልጄ ያልተሟሸው ሸክላ፣
ሕማሙን ዐይቸው ተስፋዬ መንምኖ የእምነቴ ክር ላላ፤

እናልሽ የኔ ሆድ!

ላገባሽ ያልሁትን ቃሌን አጥፌያለሁ፣
ሐሳቤን ለውጬ ሌላ ሰው ሆኛለሁ፣
ጋብቻ አስጠልቶኝ ብቸኝነት ጥሞኝ ስላገኘሁ ለኔ፣
ሰመመን ውስጥ ነኝ ቀስቃሽ የማያሻኝ የሚሆን ከጎኔ፤

ስለዚህ ናፍቆቴ!

አልመጣም፣ ጋብቻችን ቀርቶ ውላችንም ፈርሷል፣
በጋራ ያቀድነው በኔ የግል ሕልም ከተተካ ከርሟል፤

ቢሆንም ግን ውዴ!

ማፍቀሬን አልክድም መወድድሽን አልረሳም፣ አይፋቅምና መቼም ቢሆን ከቶ፣
ስንቅ ስለሆነ የተመረገ ጠጅ፣ የመንፈሴ ቀለብ የጠጣሁት ጊዜ ትዝታው ተከፍቶ።

             ታመነ ቻላቸው
             14/04/2012

Wednesday, August 21, 2019

ገድለ እስከዚያው

         
"እኔ የተፈጠርኩት ሰዎችን ለማስከፋት ነው፤ ያስከፉኝን ለማስከፋት ነው፤ ፈጣሪንም ለማስከፋት ነው።" ይላሉ።  የነተበ ልብስ ለብሰው ጥንብዝ ብለው ሰክረው እየተንገዳገዱ ይራመዳሉ። ፊታቸው በማዲያት የተሸፈነ ነው። የፊታቸው ገጽታ ያሳለፉትን የጉስቁልና ዘመን ይተርካል።
"እስከዚያው ተመልከት እባላለሁ። የእያንዳንድሽን ገመና ፀሐይ ላይ አውጥቼ እንዳሰጣ ውክልና ያለኝ ብቸኛው ግለሰብ ነኝ" ይላሉ ምን ዓይነት ቀለም እንደነበራት እንኳን ለማወቅ በምታስቸግረው ኮዳቸው ከያዙት አረቄ እየተጎነጩ። አንዳንዴ የሚከተላቸው ግሪሳ አለ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ብቻቸውን መንተል መንተል ሲሉ ይታያሉ።
ወጣቶች፣ አዋቂዎችና ሽማግሌዎች ግን ይጠየፏቸዋል። ገና ድምጻቸውን "መጣ ደግሞ ይሄ ዓለም የረሳችው አምቡላም ሽማግሌ" ሲሉ ያማርራሉ። ይሄ ግን ለእስከዚያው ቁብ አይሰጣቸውም። "ያለበት ተጉላላበት"ን ይተርቱባቸዋል። "የረከሳችሁ ስለሆናችሁ፣ ያደፈ ማንነታችሁን ለመደበቅ በኔ ያደፈ ልብስ ታፌዛላችሁ። እድፋም ሁላ! ያደፈ ጭንቅላታችሁን ከቅርጭጭቱ አላቁት። ቅርጭጭታም ሁላ! ሃሃሃሃሃሃሃሃ!..." ይሉና ወንከር ወንከር እያሉትንሽ ይራመዳሉ።
ንግግራቸው ቢያሳርራቸውም ያሽካካሉ። እስኬው ሆዬ ዘውር ይሉና "ማክላላት ላህያ አመሉ ነው። የቀራችሁ መንከባለሉ ነው። ከዘዶቻችሁ የምትለዩት በሁለት እግር በመራመድ ብቻ ነው። በቀር ቁርጥ እነወሸን! ካካካካካካካካካ ....." ይሉና እርምጃቸውን ይጀምራሉ።
ደግሞ ተመልሰው በንዴት የጦዙትን ሰዎች ያሉ። እናም "እኔ የተፈጠርሁት ሰዎችን ለማስቀየም ነው። ፈጣሪንም ቢሆን!" ይላሉ። ተንደፋድፈው በጢማቸው ይደፋሉ። ትናንትም እንደዛሬው ነበሩ፤ ነገም እንደዚያው። ይሄው ነው የእስከዚያው ገድል ጉዞ።

Monday, February 11, 2019

መግባባት ይኖረን ዘንድ ምን እናድርግ? ምንስ እንሁን?

ከዐርባ አምስት (45) ዓመታት ቀደም ብሎ የጀመረው በሐገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ የጋራ አቋም መያዝን ሽሽት ዛሬ ላይ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሷል። የአንድ ሐገር ሰዎች ተብለን እንጠራ እንጅ እርስ በእርስ የምንተያየው እንደተለያዩ ሐገራት ዜጎች ነው። እንደተለያዩ ሐገራት ብቻም ሳይሆን ታሪካዊ ጠላትነት እንዳላቸው ሐገራት ዜጎች መተያየት ከጀመርን ውለን አድረናል።

ኢትዮጵያ የሚለውን ሥም በጋራ እንጠራበት እንጂ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ የምንጋራው አቋም የለንም። በአንድ ሐገር እየኖርን፣ አንድ የይለፍ ወረቀት (Pass Port) እየተጠቀምን፣ በአንድ መንግሥት ሥር እየተዳደርን፣ ወዘተ ... የጋራችን የምንለው እና የምንስማማበት ጉዳይ ግን የለንም። 

ይኸንን ከላይ ያነሳሁትን ነጥብ የሚያስረግጡ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። በርካታ የጥቁር ሕዝብ ሐገራትና ሕዝባቸው የነጻነት ፋና ወጊ አድርገው የሚያዩትን እና እንደድላቸው አድርገው የሚቆጥሩትን የዓድዋ ድል እንኳን ልንስማማበት አልቻልንም። የእነ እከሌ ድል ነው፤ የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ ... ዓይነት የውርክብ ሐሳቦችን እየተወራወርን መናቆሪያ አድርገነዋል። ያለፈውን የኛው ታሪክ ከምንማርበት ይልቅ መበሻሸቂያ፣ መነቋቆሪያ፣ መነታረኪያ እነና የጥል ግንብ ማቆሚያ በማድረግ ላለመግባባት ስንኳትን እንውላለን።

ቋንቋን ከመግባቢያነትና ከሐሳብ መግለጫነት ነጥለን የጥልና የብጥብጥ መሣሪያ አድርገነዋል። በቋንቆቻችን ውስጥ የተከማቹ እውቀቶችን በመጋራትና በማጋራት የበሰለ ሐገራዊ አመለካከት ያለው ማኅበረሰብ ከመገንባት ይልቅ የመለያያ አጥር እየሠራንባቸው አቅጣጫው ወዳልታወቀ አድራሻ እየነጎድን ነው።  በቋንቆቻችን ውስጥ የተቀበሩ እውቀቶችን እያወጣን የጋራ የሚባል ማንነት ለመሥራት ከመጣር ይልቅ ልጆቻችን እና ታናናሾቻችን የማይግባቡበትን መንገድ ለመፍጠር የእነገሌን ቋንቋ ማወቅ የለባችሁም በማለት በእንቁላል ውስጥ እንዳለ ሽል አፍነን ለማስቀረት እንታትራለን። 

በዚህ ሁሉ ጉዟችን መግባባት የማይችል ዜጋ ለመፍጠር ተሳክቶልናል። ከተጣባን የችጋር ደከከን የሚያላቅቀን መንገድ መፈለግን ደግሞ በሚያስደምም ሁኔታ ረስተነዋል። የሰው ልጅ ያለውን በነጻነት የመሰብና የመሥራት ተፈጥሯዊ ሥጦታ በመንጠቅ ሲዋጣልን ራሳችንንም ሆነ ማኅበረሰባችንን የሚለውጥና ከድህነት አረንቋ የመምዘዣ መንገድ ለመቀየስ ግን ወገቡን እንደተመታ እባብ እየተቅመደመድን  ነው።

ለመሆኑ እንደዚህ የሆንነው ለምንድን ነው? ከዚህ የሐሳብ ድርቅና ቆፈንስ መውጣት የምንችለው እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ነው? መውጫ መንገዱን ለመፈለግስ ምን ማድረግና መሆን ይጠበቅብናል? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እያነሳን መወያየትና መሟገት አስፈላጊ ቢሆንም ረስተናቸዋል። በመሆኑም እንደግለሰብ የሚታየኝና የሚሰማኝን በዚኽች ጦማር በተከታታይ ለማቅረብ በመሞከር የድርሻየን ለመወጣት ጀምሬያለሁ። መግቢያው ይኼው። ቀጣዮቹ ክፍሎችም ይቀጥላሉ።

Tuesday, January 29, 2019

የዘንበል ዘንበል ጉዞ የት ያደርሰናል?

የኢትዮጵያን ታሪክ ስናነብም ሆነ እንደየዕድሜያችን መጠን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገዛዝ እና ለገዥዎች የነበረውንና ያለውን ዕይታና አቀባበል መረዳት ከባድ አይሆንብንም። እኔም ባነበብሁት መጠንና በሕይወት ጉዞየ በታዘብሁት መጠን ጉዳዩን የቻልሁትን ያህል ለመረዳት ጥሬያለሁ። በኔ መረዳት መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሕዝብ የአገዛዝ ሥርዓትና ገዥዎችን በተመለከተ የነበረውና ያለው አቋም "ዘንበል-ዘንበል" ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው።

ዘንበል-ዘንበል ማለት ነፋስ በሚነፍስ ወቅት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትሎ ጎንበስ ማለትን፤ እንደገናም ደግሞ ነፋሱ አቅጣጫ ቀይሮ ሲመጣ ወደተቀየረው አቅጣጫ ማጎንበስ ነው። ይህ በተፈጥሯቸው ጠንካራ ያልሆኑ የሣር ዝርያዎች ባሕሪ ነው። ሣሮች ከመነቃቀል የሚድኑት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትለው በመተኛት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብም የሣሮችን ተፈጥሯዊ ባሕሪ በመኮረጅ ከራሱ ጋር አላምዶና አዋድዶ የመጣው አገዛዝና ገዥ የያዘውን አቋም ተከትሎ እየተጓዘ የኖረና እየተጓዘም ያለ ነው። ከዚህ ባሕሪ ጋር መስማማቱንም "እንደንፋሱ አጎንብሱ" በሚል ምሳሌያዊ አነጋገር አስደግፎ የሕይወት መመሪያ እንዲሆን በማድረጉም የቀደሙትን ተከትሎ የሚመጣ አዲስ ትውልድ አገዛዝና ገዥዎችን በአዲስ መንገድ የሚያይበት መንገድ እንዳይቀርጽ ቀይዶ ይዞታል።

ዘንበል-ዘንበሉ ከሥርዓትም በላይ ግለሰብን ተመርኩዞ የተገነባ በመሆኑም አንድ ገዥ በተለየ መንገድ ሊመለክ ምንም አልቀረው እስኪባል ድረስ ለግለሰቡ ማጎብደድን ያስተማረና እያስተማረ ያለ ባሕሪ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት እንደ እንስሳ መንጋ ከፊት የቀደመው ገዥ የቀደደውን ቦይ ተከትሎ የሚፈስስ ኢ-ምክያታዊና ኢ-ተጠየቃዊ ግብስብስ አድርጎት አልፏል፤ እያለፈም ነው።

በዚህም ምክንያት ሥርዓት ገንብቶ የሚመጡ ገዥዎችን ሁሉ መምራትና መዘወር የሚያስችል መንገድ መቀየስ እንዳይቻል ሆኗል። በዚህም ምክንያት ሥልጣን የጨበጠውን ገዥ ባሕሪ ተከትለን የምንተምም ደመ-ነፍሳዊ መንጋ ሆነናል። የመጣው ሁሉ የቀደደልንን ቦይ ተከትለን የምንፈስ አስተውሎት የተሳነን ጥርቅሞች ሆነናል። የተለየ ዕይታ ያላቸውን የምንደቁስ፣ አንስተን እያፈረጥን ከመሬት የምንሰፋ ባለትንፋሽ ግዑዞችም ሆነናል።

የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን ድንብርብር እና በፍርሃት ቆፈን የተሸበብን፣ ከሥርዓት ግንባታ ይልቅ ግለሰባዊ ማንነት ላይ የምንንጠለጠል የጅምላ አስተሳሰብ ተጠቂ አድርጎናል። ሆኖም ግን ቀጥለንበታል። ዛሬም ከተቀደደልን ቦይ ባሻገር የማናይ አቅመ-ቢስ መንታሎች አድርጎናል። ራሳችንን በራሳችን የምናፍን ገራሚ ፍጡሮች አድርጎናል።

ሆኖም ዘንበል-ዘንበላችንን ለማቆም አልቻልንም፤ ወይም ለማቆም ፍላጎቱም ሆነ ፈቃዱ የለንም። ቀጥለንበታል። የት እንደሚያደርሰን ግን አናስብም። ግን ለመሆኑ ይህ የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን የት ያደርሰናል?

Monday, October 8, 2018

ወዴት ዘመም ዘመም!


አቶ ልደቱ አያሌው ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት የሁለት ክፍል ቆይታ ተመለከትኩት፡፡ ሆኖም ግን ከቆይታቸው የተረዳሁት ነገር እስከዛሬ የሚነገርባቸውን የሚያጠናክርልኝ እንጂ ንጹህነታቸውን የሚያሳይ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በተደጋጋሚ የሚያቀርቧቸው ክስ እንበላቸው ወቀሳዎች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው፡፡ አንዴ የተሻልሁ ፖለቲከኛ በመሆኔና በምክንያትነቴ ተገለልኩ፤ ሐሰተኛ ውንጀላ ተበራከተብኝ ሲሉ ቆይተው ሌላ ጊዜ ደግሞ በማንነቴ የፓርቲ ስልጣን እንዳላገኝ ተደረግሁ፣ የሻጥር ዘመቻ ተዘመተብኝ ይላሉ፡፡ በማንነቴ ሲሉም ዐማራ በመሆኔ ማለታቸው ይመስለኛል፡፡

ዐማራ በመሀኔ መገለል ደረሰብኝ የሚሉት ሰው ግን ለዐማራ ሕዝብ መብት ለመከራከር ከተቋቋመው መ.ዐ.ሕ.ድ አፈንግጠው ወጥተው የራሳቸውን ድርጅት የመሠረቱትና በፖለቲካ ውስጥ በነበሩባቸው ከ20 በላይ ዓመታት ውስጥ ዐማራው ፍዳውን ሲያይ ድምጻቸውን አጥፍተው ሲመለከቱ እና አንዳንዴም በአደባባይ ሲያሽቃብጡ ይታዩ የነበሩት ሰውዬ መሆናቸው ይገርማል፡፡ ታዲያ በማንነታቸው የሚናገሩት ሁሉ ከደረሰባቸው እስከዚህ ጊዜ ድረስ ምን አስጠበቃቸው? ለምንድን ነው ባለፉት 13 ዓመታት ውስጥ ትንፍሽ አላሉም? ስንቶቹ ዐማራ በመሆናቸው ብቻ ብዙ ስቃዮችን ሲሰቃዩ ድምጻቸውን አጥፍተው ጎሬ ውስጥ ተወሽቀው የኖሩት? ዛሬስ ድንገት ዐማራ በመሆኔ ተበድያለሁ ላመለት የሚያበቃቸው ምን ነገር አገኙ? ነው ወይስ ከአቶ መለስ ጀምሮ ሲለለምኑኝ ነበር ያሉትን ጥያቄ ተቀብለው የቀድሞው ብ.አ.ዴ.ን (የዛሬው አ.ዴ.ፓ) አባል ለመሆን ወሰኑ? ወይስ አ.ብ.ንን (የዐማራ ብሔርተኝነት ንቅናቄ) ለመቀላለቀል ዕድሉን አገኙ? ይህ ሆኖ ከሆነ ሰውዬው በሕይቀት ዘመናቸው ዐራተኛ ፓርቲያቸውን ተቀላቅለው የማውደም ዓላማቸውን ለማሳካት እየቋመጡ ያሉ ይመስለኛል፡፡

Sunday, October 7, 2018

ወይ ሕመም!

የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የመንደራችን ሙግት "ትጥቅ መፍታት እና አለመፍታት" ላይ አትኩሯል። የተለያዩ አተያዮች እና አቋሞችም እየተንጸባረቁበት ነው። ሆኖም ግን ለሙግት ማሳመኛነት እየተነሱ ካሉ አመክንዮዎች አንዱ ግን አሳማኝ ካለመሆኑም በላይ የሐሳቡን አቀንቃኞች የኢትዮጵያን ባሕል አለማወቅ ወይም እያወቁ መካዳቸውን የሚያመለክት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የመሳሪያ ባለቤት መሆን በየትኛውም የሐገራችን የገጠር ማኅበረሰብ የኩራት ምንጭና የአንድ ወንድ ሙሉ ሰውነት ማረጋገጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ከአርብቶ አደሩ እስከ አርሶ አደሩ መሳሪያ መያዝን የባሕሉ አንድ አካል አድርጎ ከመውሰዱም በላይ የመከበር ምልክቱም አድርጎ ይወስደዋል። በመሆኑም የመሳሪያ ባለቤት መሆን የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ያለ አይመስለኝም።
ስለሆነም መሳሪያን ከቤተሰቡ እንደ አንዱ ለዚያውም የብረት መዝጊያ ተብሎ እንደሚቆጠረው አድርጎ የሚወስደውን ኢትዮጵያዊ የገጠረ ነዋሪ መሳሪያህን አስረክብ ወይም ትጥቅ ፍታ ብሎ መጠየቅ የባሕሉን አንድ ጎን እርሳው የማለት ያህል የሚከብደው ነው። እንደውርደት የሚቆጠርና አስነዋሪ ተግባር እንደተፈጸመበት የሚያየውም ነው። መሳሪያ የሌለው ሌጣ መሆኑም ባሕሉ የሰጠውን የወንድነት ሚና አሳጥቶ እንደሴት የሚያስቆጥረውና በማኅበረሰቡ ዘንድም እንደፈሪና ሰነፍ የሚያስቆጥረው ነው።
ይሁን እንጅ ይህንን የማኅበረሰብ ክፍል መሳሪውን እንዲያስረክብና ትጥቅ እንዲፈታ አላደርግም የሚል ሐሳብን የተደራጀ ቡድንን ትጥቅ አላስፈታም ከሚል ሐሳብ እያነጻጸሩ ምክንያታዊ እና ትክክለኛ አስመስሎ ለማቅረብ የሚውተፈተፉ ሰዎች እየታዩ ነው። ይህም የሐገራችን ሕዝብ የገጠሩ ክፍል ማኅበረሰብ እንደመግለጫው ወስዶ የባሕሉ አካል ያደረገውን የመሳሪ ባለቤትነት ልማድ አኮስሶ የአንድ ቡድን መገለጫ ለማድረግ ከመሯሯጥ የሚተናነስ አይደለም። ለማኅበረሰብ መገለጫዎች ንቀት ከማሳየት በላይም ሽፍትነትን ማበረታታት ነው። ሰፋ ሲልም የጎሰኝነት እና የጎጠኝነት አስተሳሰብ የወለደውን እኩይ ባሕርይ እውናዊ እና ቅቡልነት ያለው አድርጎ ለማቅረብ መጣር ነው።
#እንደዚህ ዓይነት ንጽጽሮችን ትልቅ ከሚባሉ ስዎች ሲወጣ ማየትና መስማት ደግሞ ያማል።

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡