Tuesday, June 23, 2020

ምላስህን አስላ፤ ዐይኖችህን ጨፍን፤ ጆሮህንም ዝጋ!

ዛሬ በአንተ ዘመን አድጎ ተመንድጎ ስለተለወጠ የሰው ልጅ እውቀቱ፣

ጊዜው ስላለፈ ዐለምን ለማወቅ መልፋት መዳከሩ መጽሐፍ መጎተቱ፣

ማሰብ ማሰላሰል፣ መጠየቅ መመርመር ጊዜ እያባከኑ፣

ዝና ‘ማያስገኙ ሐብት አያከማቹ ገንዘብ እየሆኑ፣

ፋሽኑ አልፎባቸው ርቋቸው ሔዶ ጥሏቸው ዘመኑ፣

የሊቅነት ልኩ የአዋቂነት ሚዛን ድፍረት በመሆኑ፣

እውቅና ቀርቶብህ ሹመት እና ዝና፣

ሲያጓጓህ እንዳይኖር መባል የኛ ጀግና፣

ፍለጋህን ትተህ ማሠሡን ብራና፣

ጥያቄ መጠየቅ ሙግትን እርሳና፣

ምን ይሉኝን ንቀህ ጆሮህን ዝጋና፣

ማየት ማመዛዘን ይህ ቢሆን እንዲያ ነው … ማለትን በአንድምታ፣

አራግፈህ ውጣና በምላስህ ከብረህ ትገዛለህ እና ሊቅነትን በአፍታ፣

ውጣ በአደባባይ ማንንም ሳትሰማ ፎክር እና ደንፋ፣

ተጀነን ተንጠርበብ፤ ኮራ ብለህ ተጓዝ ደረትህን ንፋ፣

በዝና ላይ ዝና ክብር እየሰለመህ የምትነዳው ጭፍራ፣

የእውቀትህ ምሥክር ገድልህን ዘርዛሪ ብዙ እንድታፈራ፣

በየአደባባዩ፣ በየቴሊቪዥኑ እንዳሸን በፈላው ተንጎራደድ ወጥተህ በየተራ፣

ስትፈልግ ጩህበት፣ ሲያሻህ ስደብበት በልበ ሙሉነት ማንንም ሳትፈራ፣

ታግለህ ተሰውተህ፣ ያገኘኸው ስኬት ድልህ ስለሆነ፣

አፍን አስከፍቶ ድርሳንን ያዘጋ፤ መዝገብ ያስከደነ፡፡


ተረት

ተረት ልነግራቹ ነው፡፡ በጥሞና አድምጡኝ፡፡

ተረት ተረት፡፡

የመሠረት አላችሁ፡፡

ጥሩ! ተረቱን እንደሚከተለው እተርካለሁ፡፡

በሆነ ጊዜ የሆነ ቦታ ሚስቱን በጥርጣሬ የሚከታተል አንድ ባል ነበረ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ውሽማዋ ከቤቱ ሲወጣ ተመለከተና ዛሬማ የእጁን እሰጠዋለሁ ብሎ ሽመል ይዞ ተከተለው፡፡ ከቆይታ በኋላ ባዶ እጁን ወደቤቱ ተመለሰ፡፡ ሚስቱ ማጀት ውስጥ ነበረችና
“ስሚ አንቺ!” ብሎ ተጣራ፡፡
“እነሆኝ” ስትል መለሰችለት፡፡
“ያ ውሽማሽ እኮ ደበደበኝ”፡፡
“በምን?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“በሽመል” ብሎ መለሰላት፡፡
“ሽመል መያዝ አልለመደበትም ነበር፤ ዛሬ እንዴት ይዞ ወጣ?” አሁንም ጠየቀች፡፡
“እሱማ ሽመል መያዝን ከየታባቱ ያውቅና! የእኔን ሽመል ቀምቶ ነው እንጂ የመታኝ” ሲል መለሰላት፡፡

ተረቴን መልሱ፤ አፌን በዳቦ አብሱ!

Monday, June 22, 2020

እርም ለበላ ትግል ...

ምላስህ ላይ ቆሞ ሲጮህ እየዋላ፣

ትከሻህ ለይ ኾኖ በአንተው እየማለ፣
ስላንተ ሊታገል ድርጅት ፈልፍሎ እንዳሸን የፈላ፣
ብዙ ወገን አለህ ከጉሮሮህ ነጥቆ ሆዱን የሚሞላ፣
በደል ተጠይፎ ጉስቁልናህ ከብዶት፣
በመከራህ አዝኖ ያንተ ሕመም አሞት፣
አማራጭ የሚሆን ሊቀድ ዐዲስ ፈሰስ፣
ጥቃትህን ሊመክት እንባህንም ሊያብስ፣
እያሽሞነሞነ በቃላት ከሽኖ ዲስኩሩን በጆሮህ እያንቆረቆረ፣
ያንተ ወኪል ሆኖ ሲፋጭ እንደሚውል ስላንተ እያረረ፣
አደባባይ ቆሞ ሲሰብክ የሚውለው ተሳደድኩ እያለ የሚብከነከነው፣
የአንተ ማጣት መንጣት እየቆረቆረው ሰቅዞ እየያዘው እረፍት እየነሳው፣
መሆኑን ሲነግርህ ደጋግመህ ስትሰማ፣
የትግሉን መሠረት ዕቅድ እና ዓላማ፣
እምነት ጥለህበት የተነሳህለት ያቆመህ ከጎኑ፣
የምትሰዋለት እሱ በጀመረው በያዘው ውጥኑ፣

ዳግመኛም፡-
ችግርህ ተቀርፎ ትንን ብሎ ጠፍቶ አልፎ ሰቀቀኑ፣
ፋና እንዲበራልህ ጨለማህ ተገፍፎ እንዲነጋ ቀኑ፣
"ከእሱ በፊት እኔ፤ እንዲነጋ ቀኔ፣
ወገቤ እየጠና እንዲደረጅ ጎኔ፣
ግፉ እንዲያበቃልኝ የያዘኝ ኩነኔ፣
ባደግሁበት ምድር መኖር በምናኔ፣
እሱ ይከተለኝ እቀድማለሁ እኔ፣"
ያልህለት ታጋይህ ከመንገዱ ወጥቶ፣
ቆምሁለት ያለውን ዓላማውን ትቶ፣
በስምህ ነግዶ ትርፉን አደርጅቶ፣
ከፍ ከፍ እያለ ዝናው ተንሰራፍቶ፣
ዞሮ የማያይህ ሆኖ ስታገኘው ውለታን የረሳ፣
ትናንቱን ዘንግቶ እንዴትና ለምን የት እንደተነሳ፣
ቅስምህን ቢሰብረው አንጀትህ ቢከስል ቢገኝ ተኮማትሮ፣
አንተው ለራስህ ቁም እሱ ሆዱን እንጂ አያይህም ዞሮ፤

እንጂማ!
ቆሞልኛል ብለህ የምትከተለው፣ ያድነኛል ያለኸው፣
በስምህ የማለው በአንተ የሚገዘተው፣
ጥምህ የሚሰማው መራብህን የሚያየው፣
እርዛትህን ቀርፆ ምስሉን የሚይዘው፣
መሰላሉ ሆኖት እያሸጋገረው ከዙፋን ላይ ወጥቶ፣
አንተኑ ሊበላህ ቀድሞ የጋጠህን እንዳዲስ ተክቶ፣
አመዳይ ሊያለብስህ የእግሩ መርገጫ አርጎ፣
ገትኖ ሊበላህ በአንተው ወዝ አምጎ፣
ካልሆነ በስተቀር፣
እጥፍ ብሎ አንጀትህ መንምነህ እያየህ ሰውነትህ ጫጭቶ፣
ሙግግ ክስት ብለህ የለበስኸው ቆዳህ እላይህ ላይ ለፍቶ፣
ችጋር አንቆ ይዞህ ሆድህ ተሰልቅቦ ከጀርባህ ተጣብቆ፣
ማጣትህ መንጣትህ አደባባይ ወጥቶ ሲውል ፀሐይ ሙቆ፣
ሙቶ ከከረመ አጽሙ አፈር ከሆነ፣
ከዓለም ተሰናብቶ ምእት ከደፈነ፣
ሲሟገት አይውልም አስክሬን ቀስቅሶ፤
አልያም
ግዑዝ ከሆነ አካል ጆሮው ከማይሰማ ከድንጋይ ምሰሶ፣
ሲታከክ አይውልም በድንጋይ ላይ ቆሞ ድንጋይ ተንተርሶ፤
ስለዚህ ወንድም ሆይ!

እሱን ተወውና ልቡናህን አድስ፤ ራስህን አንጽ በራስህ ላይ ሥራ፣
ባንተ ላይ ተራምዶ ወደ ላይ ከወጣ ጆሮውም አይሰማ ደጋግሞ ቢጠራ፡፡

Saturday, June 20, 2020

ዛሬ እንዴት አነሰ?

ትላንት ያወደስነው ስሙን የጠራነው አክብረን በደስታ፣

ዜማ ያዜምንለት ጀግና ነህ እያልነው መጽናኛ መከታ፣

“አብሪ ኮከብ ሆኖ እየተተኮሰ፣

የነጻነት ችቦን ቀድሞ የለኮሰ፣

አጽናፍን አዳርሶ ሥሙ የነገሠ፣

ኩስምን ሁነቶችን ግርማ እያለበሰ፣

ገንኖ እያገነነ ዐለምን መዳፏን አፏ ላይ ያስጫነ፣

ከተናቁት መሀል አስናቂ እንዲወጣ ሠርቶ ያሳመነ፣”

እያልን የካብነውን ከፍ እያደረግን አውጥተን ከማማ፣

ገድየ አሞታለሁ ያልንለት በክፉ ሲነሳ ሲታማ ስንሰማ፤

 

ዛሬ፡-

ካለፈ በኋላ ጉድጓድ ውስጥ ከገባ አፈር ከለበሰ፣

አጥንቱ ከላመ፤ ሥጋው አፈር ሆኖ ገላው ከፈረሰ፣

ዐለም ከረሳችው ከውጣ-ውረዷ ከተሰናበተ፣

በሌለበት ጊዜ፣ መልስ በማይሰጠን እየተሟገተ፣

ከየጥጋጥጉ ጥያቄዎች በዙ የክስ ጎርፍ ጎረፈ፣

አርነት ያወጣ መንገድ እያበጀ ጠርጎ ያሳለፈ፣

እያልን ያወራነው ያ ሁሉ ውዳሴ ያ ሁሉ ሙገሳ፣

ሰውየው ቢጠፋ ከምኔው ተተወ ከምኔው ተረሳ?

ስሙን ያጠቆርነው ጥላሸት የዋጣው ማቅን የለበሰ፣

ከትላንቱ ግብሩ አሁን ምኑ ታጣ? ዛሬ እንዴት አነሰ?


Sunday, June 7, 2020

እንደግመል ሽንት ሁልጊዜም የኋሊት፤ አይሰለችም?

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የጉዞውን መነሻ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ብቅ ባሉት ጋዜጣዎች ጀምሮ በዓይነት እና በቁጥር እየሰፋ ዛሬ ላይ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጋዜጣ ምዕት ዓመት የሞላው ሲሆን የመጀመሪያው ሬዲዮ ጥር 23፣ 1927 ዓ.ም. ሥርጭቱን ከጀመረ 85 ዓመታትን አልፏል፤ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ጣሚያም ሥርጭቱን በ1957 ዓ.ም ከጀመረ 55 ዓመታትን ተጉዟል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ሚዲያ ዛሬ ላይ የተሳካላቸው እና ተጠቃሽ ሚዲያዎች ካሏቸው በርካታ ሀገራት ቀድሞ የተጀመረ መሆኑን ያሳያል፡፡

ዕድሜው የመርዘሙን ያህል ግን ሚዲያው እና ጋዜጠኝነቱ እያደገ ከመምጣት ይልቅ ወደ መጣበት አዙሮ እያየ የኋሊት ጉዞን የመረጠ እንዲመስል አድርጎታል፡፡ በቅርብ ዓመታት በርከት ያሉ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም የሕትመት ሚዲያዎች ተመሥርተውና ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሥራ ቢጀመሩም የሚዲያውን የቀደመ አካሔድ ከማስተካከል እና ጉብጠቱን ከማረቅ ይልቅ ከጉብጠቱ ጋር ተስማምተው መኖርን የመረጡ መሆናቸውን ማንም የሚዲያዎቹ ተካታታይ ይታዘባል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ተቋማት የአንድ ወገን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎች ሆነው መጡ፣ ዛሬም ቀጠሉበት፡፡ ለመረጃ ትክክለኝነት እና ለዘገባ ሐቀኝነት ከመጨነቅ ይልቅ እገሌ የተባለውን ባለሥልጣን እንዳላስከፋ በምን መንገድ ላቅረበው በሚል ጉዳይ የሚጨነቁ ናቸው፡፡ አዳዲሶቹም በዚሁ ገፉበት፡፡

ቁጥራቸው እየጨመረ ቢመጣም የሚዲያን ሚና እና የጋዜጠኝነት አሠራርን እያሳደጉ ከመጓዝ ይልቅ ወደኋላ የሚጎትት እና የሚያቀጭጭ አካሔድን መርጠው እየተንከላወሱ ነው፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ሥሕተታቸውን እያረሙና እየተሻሻሉ ከመሥራት ይልቅም በቡድን ተከፋፍለው የመቆራቆሻ መሣሪያ ሆነዋል፡፡ ይህም የሚዲያውን ዕድገት ወደትናንት ከመጎተቱም በላይ ሲጀመር ከነበረበት ደረጃው ዝቅ አድርጎ ወደመድፈቅ እያንደረደራቸው ነው፡፡

የፖለቲከኞች ቁርቁስ እየሰፋ ሲመጣ ሚዲያዎቹም - በተለይም ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ግብር በሚመደብላቸው ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት ሚዲያዎችም ለተቆራቋሾቹ ወግነው በመቆም በእሳት ላይ ቤንዚን እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉበት መንገድም ከእስከዛሬው አመጣጣቸው ሁሉ እየከፋና እየወረደ መጥቷል፡፡ እስከዛሬ በነበራቸው ጉዞ እውነትን በመካድ የአንድ ወገን መረጃን ማቅረብ የነበረ ሲሆን ዛሬ ላይ ግን አንዱ የሚዲያ ተቋም የዘገበውን ቆራርጦ ያልተባለን ሐሳብ እንደተነገረ አድርጎ ማቅረብ ላይ ደርሷል፡፡ የመረጃ ሽቀባው ከእርስ በርስ መረጃዎቻቸው ዓልፎ የሌላ ሀገር ሚዲያ ዘገባን መሸቀብ ላይ ደርሷል፡፡ ይህም አንድ ወይም ሁለት የሚዲያ ተቋማት ብቻ የሚገለጹበትና እና የሚወነጀሉበት ጥፋት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የሚዲያ ተቋማት የአብዛኞቹ መገለጫ ነው፡

ይህ ሁሉ ሲታይ የኢትዮጵያ ሚዲያ እና የጋዜጠኝነት አሠራር ወደፊት ከመገሥገሥ ይልቅ ወደኋላ መንሠራተትን መሥፈርት አድርጎ የሚሠራ አስመስሎታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ እና እንደሚሠሩ እየታየም በቁጥር መበርከታቸውን እና የሚፈልገውን ሐሳብ ሲያንጸርቁለት እያየ የኢትዮጵያ ሚዲያ እድገት እያሳየ እንደሆነ የሚገልጽ እና የሚሟገት ሰውም (“ምሁር”) ቁጥሩ በርከት ያለ ነው፡፡ ይህንንም እንደስኬት ወስደውት እንደድጥ በፍጥነት ወደኋላ እያንሸራተታቸው ነው፡፡

መቼ ይሆን ይህ አሠራራቸው የሚቀየረው? መቼ ይሆን ቁልቁለት ለመውረድ ከመንደርደር ይልቅ ቀበት ለመውጣት መዳህ የሚጀምሩት?


 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡