Monday, October 8, 2018

ወዴት ዘመም ዘመም!


አቶ ልደቱ አያሌው ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት የሁለት ክፍል ቆይታ ተመለከትኩት፡፡ ሆኖም ግን ከቆይታቸው የተረዳሁት ነገር እስከዛሬ የሚነገርባቸውን የሚያጠናክርልኝ እንጂ ንጹህነታቸውን የሚያሳይ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በተደጋጋሚ የሚያቀርቧቸው ክስ እንበላቸው ወቀሳዎች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው፡፡ አንዴ የተሻልሁ ፖለቲከኛ በመሆኔና በምክንያትነቴ ተገለልኩ፤ ሐሰተኛ ውንጀላ ተበራከተብኝ ሲሉ ቆይተው ሌላ ጊዜ ደግሞ በማንነቴ የፓርቲ ስልጣን እንዳላገኝ ተደረግሁ፣ የሻጥር ዘመቻ ተዘመተብኝ ይላሉ፡፡ በማንነቴ ሲሉም ዐማራ በመሆኔ ማለታቸው ይመስለኛል፡፡

ዐማራ በመሀኔ መገለል ደረሰብኝ የሚሉት ሰው ግን ለዐማራ ሕዝብ መብት ለመከራከር ከተቋቋመው መ.ዐ.ሕ.ድ አፈንግጠው ወጥተው የራሳቸውን ድርጅት የመሠረቱትና በፖለቲካ ውስጥ በነበሩባቸው ከ20 በላይ ዓመታት ውስጥ ዐማራው ፍዳውን ሲያይ ድምጻቸውን አጥፍተው ሲመለከቱ እና አንዳንዴም በአደባባይ ሲያሽቃብጡ ይታዩ የነበሩት ሰውዬ መሆናቸው ይገርማል፡፡ ታዲያ በማንነታቸው የሚናገሩት ሁሉ ከደረሰባቸው እስከዚህ ጊዜ ድረስ ምን አስጠበቃቸው? ለምንድን ነው ባለፉት 13 ዓመታት ውስጥ ትንፍሽ አላሉም? ስንቶቹ ዐማራ በመሆናቸው ብቻ ብዙ ስቃዮችን ሲሰቃዩ ድምጻቸውን አጥፍተው ጎሬ ውስጥ ተወሽቀው የኖሩት? ዛሬስ ድንገት ዐማራ በመሆኔ ተበድያለሁ ላመለት የሚያበቃቸው ምን ነገር አገኙ? ነው ወይስ ከአቶ መለስ ጀምሮ ሲለለምኑኝ ነበር ያሉትን ጥያቄ ተቀብለው የቀድሞው ብ.አ.ዴ.ን (የዛሬው አ.ዴ.ፓ) አባል ለመሆን ወሰኑ? ወይስ አ.ብ.ንን (የዐማራ ብሔርተኝነት ንቅናቄ) ለመቀላለቀል ዕድሉን አገኙ? ይህ ሆኖ ከሆነ ሰውዬው በሕይቀት ዘመናቸው ዐራተኛ ፓርቲያቸውን ተቀላቅለው የማውደም ዓላማቸውን ለማሳካት እየቋመጡ ያሉ ይመስለኛል፡፡

Sunday, October 7, 2018

ወይ ሕመም!

የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የመንደራችን ሙግት "ትጥቅ መፍታት እና አለመፍታት" ላይ አትኩሯል። የተለያዩ አተያዮች እና አቋሞችም እየተንጸባረቁበት ነው። ሆኖም ግን ለሙግት ማሳመኛነት እየተነሱ ካሉ አመክንዮዎች አንዱ ግን አሳማኝ ካለመሆኑም በላይ የሐሳቡን አቀንቃኞች የኢትዮጵያን ባሕል አለማወቅ ወይም እያወቁ መካዳቸውን የሚያመለክት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የመሳሪያ ባለቤት መሆን በየትኛውም የሐገራችን የገጠር ማኅበረሰብ የኩራት ምንጭና የአንድ ወንድ ሙሉ ሰውነት ማረጋገጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ከአርብቶ አደሩ እስከ አርሶ አደሩ መሳሪያ መያዝን የባሕሉ አንድ አካል አድርጎ ከመውሰዱም በላይ የመከበር ምልክቱም አድርጎ ይወስደዋል። በመሆኑም የመሳሪያ ባለቤት መሆን የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ያለ አይመስለኝም።
ስለሆነም መሳሪያን ከቤተሰቡ እንደ አንዱ ለዚያውም የብረት መዝጊያ ተብሎ እንደሚቆጠረው አድርጎ የሚወስደውን ኢትዮጵያዊ የገጠረ ነዋሪ መሳሪያህን አስረክብ ወይም ትጥቅ ፍታ ብሎ መጠየቅ የባሕሉን አንድ ጎን እርሳው የማለት ያህል የሚከብደው ነው። እንደውርደት የሚቆጠርና አስነዋሪ ተግባር እንደተፈጸመበት የሚያየውም ነው። መሳሪያ የሌለው ሌጣ መሆኑም ባሕሉ የሰጠውን የወንድነት ሚና አሳጥቶ እንደሴት የሚያስቆጥረውና በማኅበረሰቡ ዘንድም እንደፈሪና ሰነፍ የሚያስቆጥረው ነው።
ይሁን እንጅ ይህንን የማኅበረሰብ ክፍል መሳሪውን እንዲያስረክብና ትጥቅ እንዲፈታ አላደርግም የሚል ሐሳብን የተደራጀ ቡድንን ትጥቅ አላስፈታም ከሚል ሐሳብ እያነጻጸሩ ምክንያታዊ እና ትክክለኛ አስመስሎ ለማቅረብ የሚውተፈተፉ ሰዎች እየታዩ ነው። ይህም የሐገራችን ሕዝብ የገጠሩ ክፍል ማኅበረሰብ እንደመግለጫው ወስዶ የባሕሉ አካል ያደረገውን የመሳሪ ባለቤትነት ልማድ አኮስሶ የአንድ ቡድን መገለጫ ለማድረግ ከመሯሯጥ የሚተናነስ አይደለም። ለማኅበረሰብ መገለጫዎች ንቀት ከማሳየት በላይም ሽፍትነትን ማበረታታት ነው። ሰፋ ሲልም የጎሰኝነት እና የጎጠኝነት አስተሳሰብ የወለደውን እኩይ ባሕርይ እውናዊ እና ቅቡልነት ያለው አድርጎ ለማቅረብ መጣር ነው።
#እንደዚህ ዓይነት ንጽጽሮችን ትልቅ ከሚባሉ ስዎች ሲወጣ ማየትና መስማት ደግሞ ያማል።

Thursday, October 4, 2018

ጠያቂዋም ተጠያቂውም ሥሙን እየጠሩት ያልተገለጠው የዐማራው የሕልውና ፈተና፡-


የLTV Show አዘጋጅ ቤተልሔም ታፈሰ እና የአ.ብ.ን ሊቀ መንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ያደረጉትን ሙግት መሰል ውይይት በጥሞና አዳመጥሁት፡፡ የዐማራው ማኅበረሰብ የሕልውና ፈተና ገጥሞታል የሚለው የንቅናቄው አቋም የተመላለሱት ጉዳይ ግልጽ ሊሆንልኝ አልቻለም፡፡ ጋዜጠኛዋ ትንኮሳ ትላለች፤ ሊቀ መንበሩ ደግሞ የህልውና ፈተና ይላሉ፡፡ የሕልውና ፈተና መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይችሉ የነበረ ቢሆንም ረግጦ የማስረዳት ክፍተት አስተውየባቸዋለሁ፡፡ ጋዜጠኛዋም በበኩሏ የሕዝብ ቁጥር ብዛትን እየጠቀሰች ያህን ያህል ስፋት ያለው ማኅበረሰብ እንዴት የሕልውና ፈተና አለበት ሊባል ይችላል እያለች ትሞግታለች፡፡ ይህ ሁሉ አስፈላጊ ነበር ወይ የሚለው እንዳለ ሆኖ የሕልውና ፈተና ተጋርጦበታል ለሚለው ጉዳይ የሚከተሉትን አስረጂዎች ማየት ይቻላል፡፡
በዐማራው ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል ሲባል፡-
1.  ዐማራው በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በጅምላ ሲገደል፣ ቤት ተዘግቶበት ሲቃጠል፣ ሲፋናቀልና ከርስቱ ሲነቀል የቆየ መሆኑ፤ አሁንም እነዚህ ጉዳዮች እየተፈጸሙ መሆናቸው፣
2.  የቤተሰብ ምጣኔን እንደሽፋን የዐማራ ወጣቶች መውለድ እንዳይችሉ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው፣
3.  ወንጀል ሳይኖርባቸው ዐማራ መሆናቸውና መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በየማጎሪያ ቤቱ እየሰበሰቡ እንዳይወልድ የማኮላሸት ሥራ እየተሠራበት መሆኑ፣
4.  የመንግሥት ሥርዓትን ከሚመሩ ድርጅቶች ጀምሮ በሐገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ዐማራን ጠላትና ጨቋኝ አድርጎ የመተረክና ይህንንም ለማስረጽ በተለያዩ መንገዶች እየተሠራ መሆኑ፣
5.  በኢኮኖሚ ሥርዓቱ ግፉእ እንዲሆን የማድረድ ተግባር በፖሊሲ ደረጃ ተቀርፆ የሚሠራበት መሆኑ፣
6.  ዐማራው በሐገሩ ማግኘት የሚገባውን ማግኘት እንዳይችል፤ ከማይምነት እንዳይላቀቅና በድኅነት ሲማቅቅ እንዲኖር እየተሠራበት መሆኑ፣
7.  በተለይም ጋዜጠኛዋ ራሷ የመከራከሪያ ነጥብ አድርጋ ለማሳመኛነት ያቀረበችው ጉዳይ ዐማራው ምን ያህል የህልውና ፈተና የገጠመው እንደሆነ ለማሳያነት የሚቀርብ እንጂ እሷ እንዳለችው የሕልውና ፈተና የሌለበት መሆኑን ሊያሳይ የሚችል አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የዐማራውን ያህል በሥፋትና በከፍተኛ ሁኔታ ተሠራጭቶ የሚኖር ሌላ ማኅበረሰብ የለም፡፡ በየትኛውም የሀገሪቷ አካባቢዎች በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው አማሮች ይኖራሉ፡፡ በ2010 መስከረም ወር ላይ እን ኦቦ ለማ መገርሳ እንዳሉት በኦሮሚያ ክልል ብቻ እስከ 11, 000, 000 የሚደርሱ ዐማሮች ይገኛሉ፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም ከዚህ የሚበልጥ ቁጥር ያለው ዐማራ አለ፡፡ ይሁን እንጂ በመንግሥት ደረጃ በታቀደና በታሰበበት መንገድ የዐማራውን ቁጥር የማሳነስ ሥራ ሲሠራ ኖሯል፡፡ ብዛቱ ከሐገሪቱ ሕዝብ እስከ 50% የሚሆነውን የመሚሸፍን ሆኖ እያለ በቁጥር ሁለተኛ እንደሆነ ፐሮፓጋንዳ መነዛቱ፣ በሕዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርትም የሕዝብ ቁጥሩ እየቀነሰ መሆኑ፣
8.  በተለያዩ የሐገሪቷ አካባቢዎች በሥፋት ተሠራጭቶ የሚኖረው ዐማራ ዐማራ ነኝ ሲል ከመንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም የሚያስከለክለው በመሆኑ ምክንያት፣ ልጆቹ ቢማሩም ባይማሩም የሥራ እድል እናዳያገኙ የሚገደዱ በመሆናቸውም ምክንያት ዐማራነታቸውን ትተው በሌላ ብሔረሰብ ስም እየተመዘገቡ እንዲኖሩ እየተደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
በመሆኑም እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ ምክንያቶች ዐማራው የሐገር አልባነት ስሜት እንዲሰማውና ተረጋግቶ ሕይወትን መምራት እንዳይችል የሚያደርጉ፤ በሕይወቱም ተስፈኛ እንዳይሆንና በሐገሩ እየተሳቀቀ እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የቁጥር መቀነስን እያመጡ የአናሳ ናችሁ እኛ ከናንተ የበለጠ ጥቅም ማግኘት ይገባናል የሚሉ ትረክቶች እንዲያቆጠቁጡ እያደረገ ነው፡፡ የሕልውና አደጋ (ፈተና) ሲባልም ሙሉ ለሙሉ የመውደም ጉዳይ ሳይሆን የነበረን መሠረት የማሳጣት፣ የማኅበረሰብን ሥነ ልቡና የማዳከምና በሐገሩ ጉዳይ አንገቱን ደፍቶ ሁሌም ተበዝባዥ አድርጎ የማስቀጠል ጉዳይን የሚመለከት ነው፡፡


Wednesday, October 3, 2018

ሁሉንም በግል መነጽራችን ማየት የአብሮነት ጉዟችን ፈተና



ያለፉት ዐርባ አምስት (45) ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመጠላለፍና ጣት መቀሳሰር የተሞላ እንደነበርና እንደሆነ የሚያሳዩን በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ይህም በዛሬው ትውልድ ላይ የቀረውን ጠባሳ ሰፊ እንዲሆንና ዐዲስና የለውጥ መሠረት የሚባለው ወጣት ሃይል በከንቱ እንዲቀር አድርጓል፣ ዛሬም እያደረገ ነው፡፡

በነዚህ ዓመታት እንደአሸን የፈሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካቸውን መሠረት ያደረጉት በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ላይ በመሆኑና የነሱን የአሸዋ ላይ ውትወታ ተከትለው በነፋሱ አቅጣጫ በመመራት ታሪክ ጻፍን ያሉ ግለሰቦችም ንቅዘትን ለትውልድ የሚያስተላልፉ ትርጉም አልባና የቁርሾና የቂም ጎተራ የሆኑ ጥራዞችን አምርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሁሉም በከፋ መልኩ ይህንን የፖለቲካና የታሪክ ዕይታ በሰፊው እያቀነቀነ የነበረው ድርጅት የመንግሥትነትን ሚና ከተቀበለ በኋላ የነበሩት ለሠላሳ ፈሪ ዓመታት መነጣልና መጠራጠር በከፍተኛ ሁኔታ ያጎነቆለባቸውና አሽቶም የጎመራባቸው ጊዜያት ናቸው፡፡

ሁሉም የኔ የሚለው ጎሣ ሥር ለመጠለልና ምክንያትና ተጠየቅን ጉድጓድ ምሶ ለመቅበር ሲንደፋደፍ ራሱንና መሠረታዊ ማንነቱ ሰብአዊነትን አጉብጧል፡፡ ሁሉም ነገሮች የሚመዘኑበት መንገድም ከምክንያትና ከተጠየቅ ይልቅ ከጎሣ እና ከቋንቋ ወገንተኝነት በማስተሳሰር ሆኗል፡፡ አንደአንድ ሐገር ዜጎች ከምናስብ ይልቅ እንደበርካታ ትንንሽ ሐገሮች በምንቆጥራቸው ጎሣዎቻችን ጥላ ሥር እንድንወሸቅ ሆነናል፡፡

የራሰችንን ዜጋ ሐገርህ አይደለም በማለት ማፈናቀል ከጀመርን በርከት ያሉ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ያለፈው 2010 ዓ.ም እና የጀመርነው 2011 ዓ.ም ግን እጅግ የከፋው (ክፋቱ ከሚፈጸሙት አሰቃቂ ግድያዎች አንጻር ብቻ ሳይሆን ከነካቸው ጎሣዎች እና ከተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥርም ጭምር ነው) ይመስለኛል፡፡ ይህንነ መፈናቀል የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ከመፈናቀል በኋላ የሚደረጉ የድጋፍ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ያለበት ዕይታና የሚሰጣቸው የፖለቲካ ወገንተኝነት ትርጉምም ነው፡፡

ሐገሩ ወደዚህ ምስቅልቅል እንዴት ገባች ብሎ ከሚጠይቀው ይልቅ ማን ለየትኛው ተፈናቃይ ድጋፍ አደረገ የሚለውን ጉዳይ እያሳደደ ድጋፍ አድራጊውን አካል በጎሣና የፖለቲካ ወገንተኝነት ከረጢት ውስጥ ለመክተት የሚሽቀዳደመው ወጣት ቁጥር በብዙ እጥፍ ይልቃል፡፡ አንድ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከ2,000,000 የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው የሐገሩ ዜጎች ከኖሩበት ቀየ መፈናቀላቸውና መጎሳቆላቸው ከሚያሳዝነው ይልቅ የትኛው ዝነኛ ሰው ኬት አካባቢ ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ አደረገ? የትኛው አክቲቪስት ከየትኛው አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጉዳይ አራገበ? የመሳሰሉ ጥያቄዎችን እያነሳ ሲያራግብና አቧራ ሲያጨስ የሚውለው ወጣት ቁጥር የትየለሌ ሆኗል፡፡

መፈናቀልን ማስቆም የሚቻልበትንና ተከባብሮና ተስማምቶ መኖር የሚቻልባቸው መንገዶችን ከሚፈልገው ኃይል ይልቅ እከሌ ከዚህ አካባቢ የተፈናቀሉ ሰዎችን የረዳው እንትን ለተባለው ብሔረሰብ ቀና አመለካከት ስለሌለው ነው፤ ከእንትን አካባቢ የተፈናቀሉት ሰዎች ድጋፍ ተዥጎድጉዶላቸው ከእንትን አካባቢ የተፈናቀሉትን ቀና ብሎ የሚያያቸው ጠፋ፤ ወዘተ የሚሉ ጉዳዮችን እያነሳ እየጣለ ጉንጭ አልፋ ሙግት ሲሟገት የሚውለው ይበልጣል፡፡

ከኔ ቤት ምን ክፍተት አለ? ከሌላውስ በኩል? መፍትሔውስ ምንድን ነው? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እያነሳ ችግር የሚቀርፍ ሐሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ ሁሉም ሰው እኔ ባየሁበት መንገድ ማየት ካልቻለ ጠላቴ ነው የሚል ፍረጃ ውስጥ ገብቶ ለመሸናነፍና ለመዋደቅ ደፋ ቀና ሲል የሚታይበት ሆኗል፡፡

ሆኖስ ግን፤ ሁሌም ሰው በተፈናቀለ ቁጥር እርዳታ በማሰባሰብ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል ወይ? አንድ ጊዜ እርዳታ ያሰባሰበ ቡድን ወይም እርዳታ የለገሰ ግለሰብና ቡድንን በዚህ የነቀዘ የፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት ሰዎች በተፈናቀሉ ቁጥር እርዳታ የመስጠት ግዴታ አለበት ወይ? እርዳታ ማድረግ ችግሩን መስቆም ይችላል ወይ? የፖለቲካ ሥርዓቱ በዚህ መንገድ ከቀጠለ የሚፈናቀለው ሰው ከማይፈናቀለው የሚበልጥበት ጊዜስ ሊመጣ አይችልም ወይ? ያለበት አካባቢ የሁል ጊዜ መኖሪያው እንደሆነ ተማምኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዜጋስ ምን ይህል ነው?

በመጨረሻም ችግራችንን የበለጠ የሚያሰፉ ጉዳዮች ላይ እየተነታረክን የሚያቃቅሩን እና የበለጠ አደጋው የሚያሰፉ ጉዳዮች ላይ ተጠምደን ከምንውል መፍትሐየ ሊያመጡልን በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሐሳብ እየተለዋወጥን የአብሮነት መንገዳችንን ብንጠርግ የተሸለ ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡