Saturday, October 3, 2020
Thursday, August 27, 2020
ማንም ነህ ምንም ነህ (2)
ምናምኒት ነገር እጅህ ላይ ባይገኝ ብታጣ ብትነጣ፣
እሳት
ተለቅቆብህ ከቤት ብትሳደድ ሜዳ ብትሰጣ፣
አዝመራህም
ነድዶ ጨገሬታ ጠፍቶ ጠኔህም ቢበዛ፣
ዕድል
ፊት ብተነሳህ አሳዳጅ የሚሆን ተላትህን ብትገዛ፣
አይክፋህ ወንድሜ፣
በደል አይሰማህ መገፋት መጣልህ ፈፅሞ አያስከፋህ፤
ምክንያቱም፣
አንተ ማለት ለዓለም "ምንም ነህ ማንም ነህ"።
ወገኔ ነው ያልኸው እምነት
ጥለህበት ያደረግኸው ተስፋ፣
ቢሸሽ ቢሸሸግም ርቆ እየሔደ
ካይንህ ተተሰውሮ ከጎንህ ቢጠፋ፣
ጊዜ እየታከከ ጉልበት ቢያጎለብት
ለውድቀትህ ቢቆም አንተኑ ሊገፋ፣
ብንን ብሎ ቢሔድ ነፋስ
እንደገፋው እንደጉም ቀሎ የጣልህበት ተስፋ፣
አይክፋህ ወንድሜ፣
በደል አይሰማህ መገፋት መጣልህ ፈፅሞ አያስከፋህ፤
ምክንያቱም፣
አንተ ማለት ለዓለም "ምንም ነህ ማንም ነህ"።
የምትገብርለት
ዓመት እየጠበቅህ፣
ቆሜያለሁ
የሚልህ አንተን ልጠብቅህ፣
ካጥቂዎችህ
ቢያብር ደጋግሞ ቢክድህ፣
ዓለም ስለተወህ ዓለም ስለረሳህ፣
አይክፋህ ወንድሜ በደል አይሰማህ፣
ይልቅስ፣
ቅስምህን አበርታ
መንፈስህን አጽና፣
ቀበቶህን አጥብቅ
አንገትህንም አቅና፣
አንተን የሚታደግ
አውጪ ከፈተና፣
ከራሥህ በስተቀር
ማንም የለምና፤
አልያማ፣
ጥረህ ተጣጥረህ ታግለህ
ካላሸነፍህ ካልወጣህ አርነት፣
ዝምታህ ብርታቱ መታገስህ
ኃይል ሆኖት ጉልበት፣
ሽህ ምንተሸህ ሆኖ
ተንጋግቶ ይመጣል፣
የቅስምህ መሰበር
ውስጡን ወኔ ሞልቶት፣
ኪሱን ሊያደላድል
ሊሞላው የሱን ቤት፣
ትርፉን እያሰላ ሊሸጥ
ያንተን ሕይወት፣
ምክንያቱም፣
ራሥህ ለራሥህ መድኃኒት
ካልሆንኸው መንፈስህ በርትቶ፣
ደድረህ ካልመከትህ
ኃይልህ ተጠራቅሞ ቅስምህም ጎልብቶ፣
ዓለም አይሰማህም
ደራሽም የለህም፣
የሚገፋህ እንጂ
ደጋፊ አታገኝም፡፡
Wednesday, August 19, 2020
መንገዴን አሳይኝ
ገና ከጅምሩ፣
አንቺ ስትመሪ ስከተልሽ ኖሬ፣
ፍቅር በተባለ ገመድሽ ታስሬ፣
ያመጣኝን መንገድ ዛሬ ሳየው ዞሬ፣
ወከክ ብየ ቀረሁ አንገቴን ሰብሬ፤
መቼስ ለምን ካልሽኝ፡-
አንቺ አንቺን እያለ ተከትሎሽ እግሬ በመንደፋደፉ፣
ተስቦ ተገፍቶ አቀበቱን ወጥቶ ሲደርስ ከአፋፉ፣
በግልምጫሽ ብቻ ልቤ ሲደነግጥ ግፍፍ ሲል ቀልቡ፣
ወኔ እና ተስፋዬ በነፋስ ሽውታ ተንነው ገደል ገቡ፤
እናም፣
መውደድ እና ፍቅር ብርታት እየሰጡ እያሉኝ በል ግፋ፣
የወጣሁት ዳገት ወኔን ተመርኩዤ ታጅቤ በተስፋ፣
መልሶ ለመውረድ ጭንቅ ጥብ ሆኖብኝ የበረታ ዳፋ፣
ቁልቁል ተንደርድሬ ባናቴ እንዳልል ትክል ሔጄ እንዳልደፋ፣
ከተነሳሁበት መልሶ የሚያደርስ መሹለኪያ የሚሆን ከማጥ የሚያወጣ፣
መንገድ ምሪኝ እና ጭንቄን ልገላገል ካስገባሽኝ ዓለም ከሰመመን
ልውጣ፡፡
Tuesday, June 23, 2020
ምላስህን አስላ፤ ዐይኖችህን ጨፍን፤ ጆሮህንም ዝጋ!
ዛሬ በአንተ ዘመን አድጎ ተመንድጎ ስለተለወጠ የሰው ልጅ እውቀቱ፣
ጊዜው
ስላለፈ ዐለምን ለማወቅ መልፋት መዳከሩ መጽሐፍ መጎተቱ፣
ማሰብ
ማሰላሰል፣ መጠየቅ መመርመር ጊዜ እያባከኑ፣
ዝና ‘ማያስገኙ
ሐብት አያከማቹ ገንዘብ እየሆኑ፣
ፋሽኑ
አልፎባቸው ርቋቸው ሔዶ ጥሏቸው ዘመኑ፣
የሊቅነት
ልኩ የአዋቂነት ሚዛን ድፍረት በመሆኑ፣
እውቅና
ቀርቶብህ ሹመት እና ዝና፣
ሲያጓጓህ
እንዳይኖር መባል የኛ ጀግና፣
ፍለጋህን
ትተህ ማሠሡን ብራና፣
ጥያቄ
መጠየቅ ሙግትን እርሳና፣
ምን ይሉኝን
ንቀህ ጆሮህን ዝጋና፣
ማየት
ማመዛዘን ይህ ቢሆን እንዲያ ነው … ማለትን በአንድምታ፣
አራግፈህ
ውጣና በምላስህ ከብረህ ትገዛለህ እና ሊቅነትን በአፍታ፣
ውጣ በአደባባይ
ማንንም ሳትሰማ ፎክር እና ደንፋ፣
ተጀነን
ተንጠርበብ፤ ኮራ ብለህ ተጓዝ ደረትህን ንፋ፣
በዝና
ላይ ዝና ክብር እየሰለመህ የምትነዳው ጭፍራ፣
የእውቀትህ
ምሥክር ገድልህን ዘርዛሪ ብዙ እንድታፈራ፣
በየአደባባዩ፣
በየቴሊቪዥኑ እንዳሸን በፈላው ተንጎራደድ ወጥተህ በየተራ፣
ስትፈልግ
ጩህበት፣ ሲያሻህ ስደብበት በልበ ሙሉነት ማንንም ሳትፈራ፣
ታግለህ
ተሰውተህ፣ ያገኘኸው ስኬት ድልህ ስለሆነ፣
አፍን
አስከፍቶ ድርሳንን ያዘጋ፤ መዝገብ ያስከደነ፡፡
ተረት
ተረት ልነግራቹ ነው፡፡ በጥሞና አድምጡኝ፡፡
ተረት ተረት፡፡
የመሠረት አላችሁ፡፡
ጥሩ! ተረቱን እንደሚከተለው እተርካለሁ፡፡
በሆነ ጊዜ የሆነ ቦታ ሚስቱን በጥርጣሬ የሚከታተል አንድ ባል ነበረ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ውሽማዋ ከቤቱ ሲወጣ ተመለከተና ዛሬማ የእጁን እሰጠዋለሁ ብሎ ሽመል ይዞ ተከተለው፡፡ ከቆይታ በኋላ ባዶ እጁን ወደቤቱ ተመለሰ፡፡ ሚስቱ ማጀት ውስጥ ነበረችና
“ስሚ አንቺ!” ብሎ ተጣራ፡፡
“እነሆኝ” ስትል መለሰችለት፡፡
“ያ ውሽማሽ እኮ ደበደበኝ”፡፡
“በምን?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“በሽመል” ብሎ መለሰላት፡፡
“ሽመል መያዝ አልለመደበትም ነበር፤ ዛሬ እንዴት ይዞ ወጣ?” አሁንም ጠየቀች፡፡
“እሱማ ሽመል መያዝን ከየታባቱ ያውቅና! የእኔን ሽመል ቀምቶ ነው እንጂ የመታኝ” ሲል መለሰላት፡፡
ተረቴን መልሱ፤ አፌን በዳቦ አብሱ!
Monday, June 22, 2020
እርም ለበላ ትግል ...
ምላስህ ላይ ቆሞ ሲጮህ እየዋላ፣
ትከሻህ ለይ ኾኖ በአንተው እየማለ፣
ስላንተ ሊታገል ድርጅት ፈልፍሎ እንዳሸን የፈላ፣
ብዙ ወገን አለህ ከጉሮሮህ ነጥቆ ሆዱን የሚሞላ፣
በደል ተጠይፎ ጉስቁልናህ ከብዶት፣
በመከራህ አዝኖ ያንተ ሕመም አሞት፣
አማራጭ የሚሆን ሊቀድ ዐዲስ ፈሰስ፣
ጥቃትህን ሊመክት እንባህንም ሊያብስ፣
እያሽሞነሞነ በቃላት ከሽኖ ዲስኩሩን በጆሮህ እያንቆረቆረ፣
ያንተ ወኪል ሆኖ ሲፋጭ እንደሚውል ስላንተ እያረረ፣
አደባባይ ቆሞ ሲሰብክ የሚውለው ተሳደድኩ እያለ የሚብከነከነው፣
የአንተ ማጣት መንጣት እየቆረቆረው ሰቅዞ እየያዘው እረፍት እየነሳው፣
መሆኑን ሲነግርህ ደጋግመህ ስትሰማ፣
የትግሉን መሠረት ዕቅድ እና ዓላማ፣
እምነት ጥለህበት የተነሳህለት ያቆመህ ከጎኑ፣
የምትሰዋለት እሱ በጀመረው በያዘው ውጥኑ፣
ዳግመኛም፡-
ችግርህ ተቀርፎ ትንን ብሎ ጠፍቶ አልፎ ሰቀቀኑ፣
ፋና እንዲበራልህ ጨለማህ ተገፍፎ እንዲነጋ ቀኑ፣
"ከእሱ በፊት እኔ፤ እንዲነጋ ቀኔ፣
ወገቤ እየጠና እንዲደረጅ ጎኔ፣
ግፉ እንዲያበቃልኝ የያዘኝ ኩነኔ፣
ባደግሁበት ምድር መኖር በምናኔ፣
እሱ ይከተለኝ እቀድማለሁ እኔ፣"
ያልህለት ታጋይህ ከመንገዱ ወጥቶ፣
ቆምሁለት ያለውን ዓላማውን ትቶ፣
በስምህ ነግዶ ትርፉን አደርጅቶ፣
ከፍ ከፍ እያለ ዝናው ተንሰራፍቶ፣
ዞሮ የማያይህ ሆኖ ስታገኘው ውለታን የረሳ፣
ትናንቱን ዘንግቶ እንዴትና ለምን የት እንደተነሳ፣
ቅስምህን ቢሰብረው አንጀትህ ቢከስል ቢገኝ ተኮማትሮ፣
አንተው ለራስህ ቁም እሱ ሆዱን እንጂ አያይህም ዞሮ፤
እንጂማ!
ቆሞልኛል ብለህ የምትከተለው፣ ያድነኛል ያለኸው፣
በስምህ የማለው በአንተ የሚገዘተው፣
ጥምህ የሚሰማው መራብህን የሚያየው፣
እርዛትህን ቀርፆ ምስሉን የሚይዘው፣
መሰላሉ ሆኖት እያሸጋገረው ከዙፋን ላይ ወጥቶ፣
አንተኑ ሊበላህ ቀድሞ የጋጠህን እንዳዲስ ተክቶ፣
አመዳይ ሊያለብስህ የእግሩ መርገጫ አርጎ፣
ገትኖ ሊበላህ በአንተው ወዝ አምጎ፣
ካልሆነ በስተቀር፣
እጥፍ ብሎ አንጀትህ መንምነህ እያየህ ሰውነትህ ጫጭቶ፣
ሙግግ ክስት ብለህ የለበስኸው ቆዳህ እላይህ ላይ ለፍቶ፣
ችጋር አንቆ ይዞህ ሆድህ ተሰልቅቦ ከጀርባህ ተጣብቆ፣
ማጣትህ መንጣትህ አደባባይ ወጥቶ ሲውል ፀሐይ ሙቆ፣
ሙቶ ከከረመ አጽሙ አፈር ከሆነ፣
ከዓለም ተሰናብቶ ምእት ከደፈነ፣
ሲሟገት አይውልም አስክሬን ቀስቅሶ፤
አልያም
ግዑዝ ከሆነ አካል ጆሮው ከማይሰማ ከድንጋይ ምሰሶ፣
ሲታከክ አይውልም በድንጋይ ላይ ቆሞ ድንጋይ ተንተርሶ፤
ስለዚህ ወንድም ሆይ!
እሱን ተወውና ልቡናህን አድስ፤ ራስህን አንጽ በራስህ ላይ ሥራ፣
ባንተ ላይ ተራምዶ ወደ ላይ ከወጣ ጆሮውም አይሰማ ደጋግሞ ቢጠራ፡፡
Saturday, June 20, 2020
ዛሬ እንዴት አነሰ?
ትላንት ያወደስነው ስሙን የጠራነው አክብረን በደስታ፣
ዜማ ያዜምንለት
ጀግና ነህ እያልነው መጽናኛ መከታ፣
“አብሪ ኮከብ ሆኖ እየተተኮሰ፣
የነጻነት ችቦን ቀድሞ የለኮሰ፣
አጽናፍን አዳርሶ ሥሙ የነገሠ፣
ኩስምን ሁነቶችን ግርማ እያለበሰ፣
ገንኖ እያገነነ ዐለምን መዳፏን አፏ ላይ ያስጫነ፣
ከተናቁት መሀል አስናቂ እንዲወጣ ሠርቶ ያሳመነ፣”
እያልን
የካብነውን ከፍ እያደረግን አውጥተን ከማማ፣
ገድየ
አሞታለሁ ያልንለት በክፉ ሲነሳ ሲታማ ስንሰማ፤
ዛሬ፡-
ካለፈ
በኋላ ጉድጓድ ውስጥ ከገባ አፈር ከለበሰ፣
አጥንቱ
ከላመ፤ ሥጋው አፈር ሆኖ ገላው ከፈረሰ፣
ዐለም
ከረሳችው ከውጣ-ውረዷ ከተሰናበተ፣
በሌለበት
ጊዜ፣ መልስ በማይሰጠን እየተሟገተ፣
ከየጥጋጥጉ
ጥያቄዎች በዙ የክስ ጎርፍ ጎረፈ፣
አርነት
ያወጣ መንገድ እያበጀ ጠርጎ ያሳለፈ፣
እያልን
ያወራነው ያ ሁሉ ውዳሴ ያ ሁሉ ሙገሳ፣
ሰውየው
ቢጠፋ ከምኔው ተተወ ከምኔው ተረሳ?
ስሙን
ያጠቆርነው ጥላሸት የዋጣው ማቅን የለበሰ፣
ከትላንቱ
ግብሩ አሁን ምኑ ታጣ? ዛሬ እንዴት አነሰ?
እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡
-
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣ በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡ ማረሻና ድግር፣ ሞፈርና ቀንበር ተሸክሞ ወጥቶ የሚታገል ካፈር ማጭድና መንሹን ማርገቢያ ላይዳ ችግሩን ሸክፎ ከትቶ በአኩፋዳ ጋራው...
-
ያለፉት ዐርባ አምስት (45) ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመጠላለፍና ጣት መቀሳሰር የተሞላ እንደነበርና እንደሆነ የሚያሳዩን በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ይህም በዛሬው ትውልድ ላይ የቀረውን ጠባሳ ሰፊ እንዲሆንና ዐዲ...
-
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የጉዞውን መነሻ በ19 ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ብቅ ባሉት ጋዜጣዎች ጀምሮ በዓይነት እና በቁጥር እየሰፋ ዛሬ ላይ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጋዜጣ ምዕት ዓመት የሞላው ሲሆን የመጀመሪያው ሬዲ...