Thursday, June 22, 2017

ጎጃም ኑራ ማሬ (ክፍል 1)

(የዘፈኑ ‹ሙዚቃው› አጠቃላይ ሁኔታ)
የት ነበር ያኖርኩት ቀፎዬን ስል ኖሬ
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኑራ ማሬ፡፡
ብራናየ አንች የልጅነት ጓዴ
ተረሳሽ ወይ የሳቱ ዳር ተረት ባንዴ::

በዘብህ የተሰደደው ፍቅሩን (ሰብለወንጌል መሸሻን) ጎጃም አስቀምጦ ነው፡፡ ጎጃም ተስፋው አለች፡፡ ተስፋው ተከትላው መምጣት አልቻለችም፡፡ ትመጣለች ብሎ እየጠበቃት የውኃ ሽታ ሆና ስትቀርበት ፍቆት ሽታውን ሊፈልጋት ተመልሶ ወደ ጎጃም ጉዞ ጀመረ፡፡ የጎጃምን ምድር ዳርቻውን እንደረገጠ በሽፍቶች ተደብድቦ መራመድ እንኳን አቅቶት መንገድ ላይ ወድቆ አንዲት ሴት ታገኘውና ታስጠጋዋለች፡፡ በተጠጋበት ቤት ተስፋው ተቆራምዳ፣ መንኩሳ ቢጫ ልብስ ለብሳ ያገኛታል፡፡ በጣዕርና በሳቅ መሐል ሆኖ ሕይወቱ ታልፋለች፡፡

ይህ ፍቅር እስከመቃብር የተሰኘው ድንቅ መጽሐፍ የሚተርክልን ጉዳይ ነው፡፡ ይሀንን ነገር ቴዎድሮስ ካሳሁን በሙዚቃ ሰርቶ ሲያመጣልን ፍቅር እስከመቃብር የያዘው አድማስ ብቻ እንዲበቃው ሆኖ የቀረበ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ይህንን እምነቴን ያስረዱልኝ ዘንድ ሁለት ነገሮችን እጠቅሳለሁ (ለጊዜው)፡፡

1.     1.  ዜማው፡- ሲጀምር ከቅዳሴ ዜማ ይነሳና ወደሚያስደልቅ ደማቅ የጎጃም ባሕላዊ ጭፈራ ምት ይሸጋገራል፡፡ ቅዳሴ በጎጃም ማኅበረሰብ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ከገበሬው እስከ ካህናቱ ቅዳሴ ቢታጎል መዓት የሚወርድባቸው፤ አምላካቸው ወደ ምድር መጥቶ ተሰቃይቶ የሚሞት የሚመስላቸው ናቸው፡፡ ቅዳሴ ከተጀመረ በኋላ ማንም እንዳይገባ የደጀ ሰላማቸውን በር ግጥም አድርገው ዘግተው በጥሞና የሚከታተሉ፣ በሩ ተከፍቶ ሰው ጥሶ ከገባ አካላቸው የተረገጠ ያህል ስቅቅ የሚላቸው፣ መላእክት ወደምድር መጥተው ለአምላካቸው እየሰገዱና እያሸበሸቡ እያለ ተረገጡ ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ሥለሆነም ዜማው በቅዳሴ መጀመሩ ስራው ማኅበረሰቡን በጥልቀት ከማየትና ከመረዳት የመነጨ መሆኑንና እጅግም በጥንቃቄ የተሠራ መሆኑን ያሳያል፡፡

ዜማው በቅዳሴ እንጀመረ በዚያው አይቀጥልም፡፡ አንጀት ወደሚበላ ነገር ግን ወደለቅሶ በሚመራ ደማቅ ዜማ ይሸጋገራል፡፡ ጎጃሞች የሚደልቁት ሲደሰቱ ብቻ አይደለም፤ ሲያዝኑም አንጂ፡፡ ጎጃሞች ሰው ሲሞት በየአድባሮቻቸው አደባባይ በመገኘት ሙሾ ያወርዳሉ፡፡ ሙሾው እጅግ ግጥም አዋቂነታቸው በተመሰከረላቸው  አስለቃሾች እየተመራ በረገዶ ታጅቦ በእናቶች ደረት ድቂ እየደመቀ የተለየ የሐዘን ስሜትን የሚፈጥር ዜማ ይፈጥራል፡፡ ዜማው እንጉርጉሮም ድለቃ የሚመስል ድምፀትም ያለው ነው፡፡ ይህ ድምፀት ነው በቴዎድሮስ ካሳሁን “ማር እስከ ጧፍ” ሙዚቃ ውስጥ የሚስተዋለው፡፡

ጎጃሞች በደስታቸው ወቅት መንደራቸው ምድርን በሚያንቀጠቅጥ ድለቃ ይቀልጣል፡፡ አዝመራ ከመሰብሰብ እስከሌሎች ማኅበራዊ ሁነቶች ባለው የእርስበርስ ግንኙነታቸው የደመቀ ጭፈራ ከመንደሮቻቸው አይጠፋም፡፡ ጧፍ ውስጥ የሚገኙት ቁጢቶች ሰም አስተባብሮ እንዳያያዛቸው ጎጃሞችን አጣምሮ የሚያያይዛቸውና ኑሯቸውን በሕብረት እንዲመሩ የሚያደርጋቸው ፍቅር ነው፡፡ ያ ፍቅራቸው ደግሞ የሚገለጸው ልብን በሚያሞቀው ዜማቸው ነው፡፡ ዜማ የሁሉ ነገራቸው መግለጫ መሣሪያ ነው፡፡ ዓይነቱ ይለያይ ይሆናል እንጂ፡፡

22. በግጥሙ ውስጥ የሚጠቀሱት ቃላት፡- በዚህ ሙዚቃ ግጥም ውስጥ ቴዎድሮስ ካሳሁን የተጠቀማቸው ቃላት እጅጉን ለጎጃምና ጎጃሜዎች የቀረቡ ናቸው፡፡ ይህም ከያኒው ሥራውን ለመሥራት ምን ይህል ስለማኅበረሰቡና ማኅበረሰቡ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ስለተጻፈው ፍቅር እስከመቃብር መጽሐፍ በጽሞና አንዳሰላሰለ የሚያሳይ ነው፡፡ “የፀበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል” ይላል የዘፈኑ ግጥም ጀመሪያ ስንኝ፡፡ ፀበልና እንኮይ ከጎጃም ማኅበረሰብና ልጆች ጋር ከፍተኛ ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡ ፀበል በጎጃም ማኅበረሰብ ዘንድ እጅግ የተከበረና ከማንኛውም ዓይነት የሕክምና ተግባር ቅድሚያ የሚሰጠው ፈውስ የማግኛ መንገድ ነው፡፡ እናም ከያኒው ሰብለወንጌልን ለመግለጽ የተጠቀመው፡፡

ኑራ-በተለመደው ዐማርኛ የሆነ ቦታ (ሥፍራ) ቆይታ የሚል ፍቺ አለው፡፡  ሌላ ተጨማሪ ፍቺም ይሸከማል፡፡ አንድም የሆነ ቦታ እያለች (ሳለች) ነው ለካ… የሚል፤ አንድም ለካ እሷ ናት እንደማለት፡፡ በቴዲ አፍሮ ዘፈን ተደጋግሞ የሚጠራው ቃልም “ጎጃም ኑራ ማሬ” የሚል ነው፡፡ ጎጃም “ጎጃም ኑራ ማሬ” ሲል አንድም በዛብህን የወከለው ሰው ሰብለ ወንጌልን ሸዋ ሲጠብቃት እሷ ግን ጎጃም ያች መሆኗን አመልካች ነው፡፡ አሊያም የኔ መድኃኒት ጎጃም ነች እንደማለትም አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡

ማር ከጣፋጭነቱ በተጨማሪ መድኃኒትነቱ ፍቱን የሆነ መሆኑ የታወቀ ሐቅ ነው፡፡ (ይቀጥላል-- ተጠናክሮ)


Thursday, June 8, 2017

ጎጃም ኑራ ማሬ (ተከታታይ ጽሑፍ)
መግቢያ
የጸበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል
ተሸፍና ዋርካ ከልሏት የዛፍ ጠል፤
ጸበል እንደማንኛውም ውኃ አይደለም፡፡ በውኃነቱ ውኃ ቢሆንም በግብሩና በክብሩ ግን የተለየ ነው፡፡ ያ ውኃ ያበቀላት እንኮይ ደግሞ የተቀደሰች ነች፡፡ ግጥም በትዕምርት የደመቀ ነውና ትዕምርታዊ ውክልናውን እያመሰጠሩ መጓዝ መጀመር ያለበት ከመጀመሪያዋ የግጥሙ መስመር ጀምሮ ነው፡፡ እንኮይ በጎጃም ወጣቶች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነ ጣፋጭ ፍሬ ነው፡፡ የጣዕም መለኪያ ነው፡፡ በግጥሙ ውስጥ የቀረበችው እንኮይ ደግሞ የጸበል ዳር ነች፡፡ ማንም እንደፈለገ የማይነካት፤ የደረሰ ሁሉ የማይቀጥፋት፡፡ እንኮይዋ ሰብለወንጌል ነች፡፡ የንጹህ ዘር ከሚባለው የወቅቱ ማህበራዊ መዋቅር አካል ካንዱ የተወለደች፡፡ ማንም ቢፈልግ በቀላሉ የማያገኛት፤ በአጥር የተከበበች ግን በቅድስና የቀመጠች፡፡ ወንዙ በዙሪያዋ ያለው ተፈጥሮ ነው፡፡ ከምትበላው እስከምትጠጣው፣ ከምትለብሰው እስከምትቀመጥበት አቀማጥሎ የያዛት ማኅበረሰብ፡፡ ውበቷን ጠብቃ ደምቃ እንድትታይ ያደረጋት ማኅበረሰብ፡፡
ሁለተኛው ስንኝ ላይ ስንደርስ “ተሸፍና ዋርካ …” የሚል ሐረግ እናገኛለን፡፡ ዋርካ በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ፣ የተከበረ፣ … የሚባል ነገርን የሚወክል ግስም ያለው ዛፍ ነው፡፡ ዋርካ ሥር የሚበቅሉ ማናቸውም ዓይነት እጽዋት ወይ ኮስምነው ይቀራሉ፤ አሊያም ውበታቸው በዘርፋፋው የዋርካው ቅጠል ተከልሎ ማንም ሳያየው ይኖራል፡፡ የስንኙ ሁለተኛ ሐረግም የሚለው “… ከልሏት የዛፍ ጠል” አይደል፡፡ ዛፍ ተጠግቶ የወጣ ማናቸውም ተክል ቀጭጮ የሚቀር ነው፡፡ ኮስማና፡፡ እንደፈለገ ማደግም ሆነ መወዛወዝ የማይችል የትልቁ ዛፍ ጥገኛ ነው፡፡ ዛፉ ሲዘም አብሮ የሚዘም ዛፉ ጸጥ ሲል አብሮ ጸጥ የሚል በራሱ ትንፋሽ የማይንቀሳቀስ አሳዛኝ ተክል ይሆናል፡፡ ዛፉ ጨካኝ ከሆነ ድራሹ ይጠፋል፡፡ ሰብለወንጌልን የከለላት ዛፍ የወላጆቿ የጨዋ ዘር ነን፣ ከኛ የሚጋባ ከኛ የሚመጣጠን ጨዋ የጨዋ ልጅ እስካላገኘን ለማንም አንድርም የሚል፤ ከወደደችው ጋር ብትሔድ አስደፈረችን ብሎ ከሰውነት ወደዕቃነት አውርዶ የሚያስጥል ጎታች ማኅበራዊ እሳቤነው፡፡ ሰብለ በዚህ ጎታች አስተሳሰብ ምክንያት ውብ እያለች የጠወለገች፤ ኮኮብ እያለች ብርሃኗ የደበዘዘ ጉብልነች፡፡ ደማቋ ኮኮብ ሰብለ በተንሰራፋው ደንቃራ ማኅበራዊ ሥርዓት ምክንያት የተከደነች፤ መጫዎት ሲያምራት በትልቁ ዋርካ ተከልሎ ነፋስም ብርሃንም እንደተነፈገው ተክል ሁሉን የተከለከለች መንታላ ፍጡር፡፡
ቴዎድሮስ ካሳሁን በዚህ ሥራ ላይ መጠበቡ የጀመረው እንግዲህ ከመጀመሪያው የግጥሙ ስንኝ ከመጀመሪያው ሐረግ ጀምሮ ነው፡፡ እያንዳንዱ የዘፈኑ ግጥም ስንኞች ሐረግ ትዕምርት ያነገበ ነው፡፡ እያንዳንዱ ስንኝ መስመር በመስመር መተንተን የሚችል፡፡ እያንዳንዱ የግጥሙ አንጓ አንድ ትልቅ መጽሐፍ ሊወጣው የሚችል ትንታኔ የሚሠራበት በትዕምርት የተለወሰ ቋንቋ፡፡ እያንዳንዱ መስመርበ ቅመም ያበደ፡፡ እያንዳንዷ ቃል ተፈልቅቃ ስትዘረጋ ረጅም ርቀት መጓዝ የምትችልበት፡፡ በረቀቀ መንፈስ የረቀቀ፡፡ ሳስበው ሳስበው የዚህ ዘፈን ግጥም ሲጻፍ ቴዎድሮስ ብቻውን አይደለም፡፡ አንዳች የጥበብ ዛር እጁን ይዞ እየጎተተ እንደዚህ ብለህ ጻፍ እያለ ሲመራው የነበረ ይመስለኛል፡፡ እሱ ራሱ እንደተናገረው የዚህ ዘፈን ግጥም የተጻፈው በአንድ ምሽት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ትዕምርት የታጨቀበት ግጥም እንዲህ በቅጽበት በአንድ ምሽት ተጽፎ ይጠናቀቅ ዘንድ ምትኃታዊ መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ ያ የመንፈስ ምትኃት ከቴዎድሮስ አእምሮ ስር ተወሽቆ እያንዳንዷን ቃል ከአርያም እየመዘዘ፤ እያንዳንዷን ሥንኝ በማር እየለወሰ እየጋተው ካልነበረ በስተቀር ይህንን አስማት አከል ግጥም በአንድ ምሽት በሰው አእምሮ መጻፍ እጅግ የሚከብድ አንዳንዴም የማይታሰብ ቢታሰብም በዚህ ዓይነት ነዛሪ መንፈስ ለብሶ ማቅረብ የመቻል ነገር አምላክ አከልነትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡
እንደኔ ቴዎድሮስ ካሳሁን የግጥም ችሎታው የመጠቀና የተመሳጠረ መሆኑን ለመመስከሁሉንም ዘፈኖቹን መስማት፣ አሊያም የዚህን ዘፈን ሙሉ ግጥም ማጣጣም የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ሁለት ስንኞች ብቻ ማስመስከሪያ ሊሆኑት ይችላሉ፡፡


Saturday, April 22, 2017

መውደድ ቢያደማኝም ….

ዐይንሽ ደምቆ የሚታየኝ ካረፍኩበት የሚጠቅሰኝ፣ የሚጠራኝ
ልቤ ባዶ፣ ዐይኔ ምኞት ስለያዘው መንፈሴን ስለራበኝ
እንጂማ
አንቺን እንድጠላሽ ከምውድሽ በላይ ነበረኝ ሰበቡ
ሕማም ቢሆንብኝ በደልን ማመንዠክ፣ ደጋግሞ ማሰቡ
እርም ይረመኝ ብየ አራግፌ ጣልኩት
አንቺን እንዳላጣ አምርሬ ጠላሁት
ታዲያስ
አንቺን ትቼ
ፍቅሬን ተጣልቼ
ውዴን ረስቼ
ፍቅርሽን ሸሽቼ
መግቢያዬ የት ሊሆን የትአባቴስ ልደርስ
ምንስ እያሸተትኩ ምንስ ልተነፍስ
መዓዛሽን ርቄ
መውደዴን ደፍቄ
ሳይሽ መደንበሩን መርበትበት መራዱን ለማን አቀብዬ
ብስክስክ ገላሽን ተሰባሪ መሳይ ወዴት አስቀምጬ ማን ይጠብቅ ብዬ፡፡

Sunday, November 27, 2016

ጥሩ መጽሐፍ ማንበብ

መጻሕፍት ጥሩ ሆነው ሲቀርቡ አእምሮን ያድሳሉ፡፡ የንባብ ፍላጎትን ከተወሸቀበት ሥርቻ  መንጥቀው ያወጡታል፡፡ በተለይማ በሕይወት ልምድ ታጅበው ሲቀርቡልን፡፡
የፕሮፈሰር ሽብሩ ተድላ "ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ፤ የሕይወት ጉዞና ትዝታየ" ምንም ዓይነት የተደበተ ስሜት ውስጥ ቢሆኑ የሚኮረኩር ነው፡፡ ከታሪካዊ መረጃዎች ሐብታምነቱ እስከ ባሕል መገለጫነቱ ይህ ነው በሚባል ዋጋ ሊተመን የሚችል አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ አካባቢ ማኅበረሰብ አንዱ ከሆነው ከጎጃም ማኅበረሰብ ለማትተዋወቁ ያስተዋውቃችኋል፤ ለምትተዋወቁ ትውውቃችሁን ያደረጃል፡፡ ላደጋችሁበት ደግሞ የትዝታ መቆስቀሻ ይሆናልና አንብቡት፡፡

Wednesday, June 1, 2016

ሰው ነበር!




በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ማረሻና ድግር፣ ሞፈርና ቀንበር
ተሸክሞ ወጥቶ የሚታገል ካፈር
ማጭድና መንሹን ማርገቢያ ላይዳ
ችግሩን ሸክፎ ከትቶ በአኩፋዳ
ጋራውን የወጣ ቁልቁል የወረደ
ለግዜር እንግዳው ሲል ጠቦቱን ያረደ
የደግነት አባት፣ የልግስና እናት መሆኑን ያሳየ
ዕውቀትን ለማግኘት ማጥን የቀመሰ አሳር ችግር ያየ
የጥንካሬ ምንጭ የጀግንነት አርማ
ሐሩር ተቋቁሞ ጭንጫውን ያለማ
በቆንጥር በእሾሁ በጋሬጣው አልፎ
ድንበር የጠበቀ ለዘብ ተሰልፎ
መንገድ የጠረገ በዋሻ ቀዳዳ ማለፊያ ያመጣ
ሊወር ሊበርዘው የዘመተበትን መድረሻ ያሳጣ
አርበኛ መልምሎ ፈትኖ አንጥሮ ያወጣ
ጀግናስ ነበር ባገር የሚታወስለት ከውስጡ ያላጣ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
መልካም ሰው ያፈራ መልካም የተባለ
ምስክር ያላጣ ማንነቱን ገፍቶ ወርውሮ ያልጣለ
በፍልፈል ኵይሳ በቀበሮ ጉድጓድ ገብቶ ተወሽቆ
ጥበቡን ያሳየ ዕፁብ ሕንፃ ሠርቶ አለትን ፈቅፍቆ
መከራን ተሻግሮ ጋሩን አሳልፎ ደስታን ያነጠፈ
የቆሸሸ ለብሶ የሚበላው ቢያጣም ውስጡ ያላደፈ
ውሽንፍር ወጀቡን በጥበብ ያለፈ
ባለደማቅ አርማ ኰኰብ የለበሰ
አካሉ ያነሰ ልቡን ያነገሠ
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ሀ ብሎ ጠንቁሎ አንድ ሁለት እያለ ከድንጋይ ቆልሎ
ከካብ የዘለለ በግርማው ያማረ ትልቅ ሐውልት ላይ ሰንደቅ አሰቅሎ
በልቡ ባሕር ላይ ባንሳፈፈው ጀልባ መቅዘፍን ተምሮ
ከባሕሩም ወዲያ ከባሕሩ ወዲም ያገኘውን ሁሉ ቀምሞ መርምሮ
ሞት ብቻ ሲቀረው ሁሉን አሸንፎ
ያለፈ ሰው ነበር በሕሊናው አርፎ፡፡
       በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
      በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
በ ብሎ ደርድሮ በበገና ክሮች መንፈሱን አድሶ
ክራሩን ከርክሮ መሰንቆ ገዝግዞ አንጀቱን አርሶ
በሙዚቃው ቃና በጭፈራው ድምቀት በእልልታው ታጅቦ
ላለመደራረስ እየተማማሉ፣ ቆርጠው የነበሩን ያዋለ ሰብስቦ
ባለጎፈር ጀግና ባለለምድ ጎስቋላ
ባለበረት ንብረት ባለዕዳ መንታላ
ባለዐደራ ሆኖ ይልሰው ሳይኖረው ዐደራ ያልበላ
አጥር ተሸካሚ ሰዋሰው ደገሌ ባለሁለት ባላ
ችንካርም ምሰሶ ወጋግራ እየሆነ ጎጆ የቀለሰ
በጎረቤት ንጣት ውድቀት የቆዘመ እንባ ያለቀሰ
ቁስሉ ሳይጠግለት ሕማሙ ሳይለቀው ገመምተኛ ሳለ
የሐገሩን ጥሪ በፍርሃት በክህደት በእብለት ያልጣለ
በተፈለገበት መስክ ቀድሞ የተገኘ
ባልተማረ አንደበት ቅኔ የተቀኘ
የሆድ ነገር ብሎ ለሆድ ያልተገዛ ለሆድ ያላደረ
እንደ ልቡ ፈቃድ በሕሊናው ምሪት የጣረ የጋረ
ባለ-ስም ስም-አልባ ባለክብር ክብር ያጣ
ሐብት ሞልቶ ተርፎት ችግር ያራቆተው ቀኝ እጁ የነጣ
በነጣ ቀኝ እጁ ልሒድ ልሒድ ያለ ግራውን የቀጣ
ፍፁም ፈውስ ያገኘ አእምሮው ያረፈ ከሕሊና ቁጣ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
በፈዘዘ ሌሊት ብርሃን ፈንጥቆ ጨለመ ገፋፊ ጭላንጭል ፈንጣቂ
ከአንበሳ መንጋጋ ስጋ ያስለቀቀ ከነብር ጥፍሮች ሥር ሙዳ ተናጣቂ
እኔ ከሞትኩ ብሎ ሰርዶ ያልነቀለ
አሻራ የሚሆን ባለግርማ ሐውልት በጁ የተከለ
ሳይንስ ያላወቀ ሳይንስ ያረቀቀ
ጥበብ ያነገሠው በጥበብ የላቀ
ክክፋት ውቅያኖስ በደግነት ታንኳ ተንሳፍፎ የወጣ
ከመደንቆር ባሕር በዋና መፍጨርጨር አምልጦ የመጣ
በጨለማ ዋሻ አተምትሞ ሮጦ መንገድን የመራ ተስፈንጥሮ ወጥቶ
በእርዛት ዘመኑ ወገኑን ያልተወ ክብር ያለበሰ አጣፍቶ ድሪቶ
ችጋር ቸነፈሩን በማጎንበስ አልፎ ለጭቆና ቀንበር ያላጎነበሰ
መገዛትን ሸሽቶ መግዛት ያልመረጠ ፍርድ ያላስነከሰ
ጨለማ ሰባሪ ተወርዋሪ ኰኰብ ጅራት ያበቀለ ለእንቅልፍ ያልታደለ
መታፈን ያልገታው የጠቆረን ሰማይ በብርሃን መስመር እኩል የከፈለ
ወቀሳና ትችት ተንኰልና ሸርን ዐይቶም እንዳላየ ሰምቶም እንዳልሰማ
በደግ! ያለፋቸው መንገድ የጠረገ ያልተወላገደ ያረቀ ጠማማ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ረግረጉን አልፎ ከትልቅ ጋራ ሥር ጎጆ የቀለሰ
ያረጀ፣ የወደቀውን ቤት መልሶ ያቆመ በደሙ ያደሰ
ለቆመለት ጉዳይ አንገቱን የሰጠ ደሙን ያፈሰሰ
በጽናት ያደረ ፈተና ያልጣለው እ! ብሎ ካንጀቱ ውስጡ ያለቀሰ
መንፈሱ ያልላመ ክንዱ ያልደቀቀ
ነውር ያላሸነፈው ክብሩ ያልወደቀ
ወንድሙን እህቱን ሕዝቡን ያልሰረቀ
ወገንማ ነበር ራሱን አዋርዶ ሐገር የጠበቀ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
11/09/08
አርባ ምንጭ፣ ሲቀላ፡፡

Wednesday, April 27, 2016

ያላለቀው ሕመም

ብሶት
                                                    አሻግሬ እንዳላይ ድርገት ነው ጨለማ
                                                    ዐይን የሚያስጠነቁል ድምጽ የማያሰማ
የቅርቡን እንዳላይ ዐይኔን ይወጋኛል ጆሮዬን ደፋፍኖ
 ዕውቀት ገደል ገብቶ ማስተዋል ታፍኖ ድንቁርና ገኖ፡፡
••••••••••
ሐገሬ ውስጥ የምኖር አልመስልህ እያለኝ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ፍርሃትና ስጋት የሞላበት ሆኗል፡፡ በየእለቱ ጥዋት ተነስቶ የሚደርሰው ጸሎት ‹‹ኣባክህ ጌታየ በፌደራል ጡንቻ ከመቀጥቀጥ ጠብቀህ፣ ከደህንነት እንግልት ሰውረህ አውለህ አግባኝ›› የሆነ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንኳን ጸሎት ሞክሬ የማላውቀው ልለው ይዳዳኛል፡፡ ሁሉም ነገር ‹‹የከንቱ ከንቱ፣ ከንቱ ነው›› የተባለው ለሐገሬ የዛሬ ሁኔታ እንደሚስማማ ጥርጣሬ የለኝም፡፡
አገር በሙሉ ፈዝዞ ማየትን ያህል የሚያም ነገር አለ ብየ አላምንም፡፡ በየመስኩ የተበተኑ ሰዎች ሁሉ ድንቁርናን አባታቸው ውንብድናን እናታቸው ያደረጉ በመሆናቸው ሐገር ጥቁር ለብሳለች፡፡ ዐይኗን ጥሎባታል፡፡ ሁሉን ነገሯ የሕልም ሩጫ ሆኖባታል፡፡ የሚታየው ነገር ሁሉ ተስፋ የሚያሳጣ፣ ወደፊትም ወደኋላም ለመንቀሳቀስ መፈናፈኛ የሌለው ሆኗል፡፡
ታሪክ ያለው ሕዝብ ዛሬ እንደተወለደ ተቆጥሮ ‹‹የሕዝቦች ልደት›› የሚል ዶክመንታሪ ፊልም ሲሰራበት፣ ክብር የሚገባው ሰብአዊ ፍጡር ከእንስሳ ያነሰ ኑሮ ሲኖርና የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ከውሻ ጋር ሲታገል ከማየት የበለጠ ምን የሚያም ነገር አለ? ሐገር የገነባን ታላቅ ንጉሠ ነገሥት እንደ ወራሪ የሚቆጥር ወንበዴ ስልጣን ላይ ጉብ ብሎ በታላቅ ሕዝብ ላይ ሲፈነጭ፣ ደንቆሮ የወረዳና የቀበሌ ካድሬዎች የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ፖለቲካዊ ስልጠና ሲያሰለጥኑ ሲታይ፣ ንባብ ጠላቱ የሆነ ሰው የዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ አስተማሪ ሆኖ ሲያደነክር ሲታይ፣ የእውቀት ማቅኛና መሸመቻ የሆነ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚደንትነት የሚመራ ሰው መጽሐፍት እንዲቃጠሉ አፉን ሞልቶ ሲናገር ሲሰማ፣ … ምን የማይቆጠቁጥ ነገር አለ፡፡
ዓለም የእንስሳት ነጻነት ያሳስበኛል የሚሉ ምሁራን ብቅ እያሉባት ባለበት ጊዜ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ መጽሐፍ እያሳተሙ የሚቸበችቡባትን ሐገር ማየትና እሷ ውስጥም መኖር፣ አገር እመራለሁ ብሎ ዙፋን ላይ ፊጥ ያለ ሰው ተራ የሚባል ወንበዴ አንኳን ሊያወጣቸው የሚቀፉ ቃላትን ከአፉ ሲመዝ እንደመስማት የአንድን ወጣት ልብ የሚያደማ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
በዚች በኛ ሀገር ውስጥ ከሠላሳ በላይ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚጠቀሙበት ሥርዓተ ትምህርት ተመሳሳይና የየተቋማቱን ሉአላዊነት የሚፈታተን ነው፡፡ ተቋማቱ በአካባቢ ተወላጅ ይተዳደሩ የሚለው ምናልባትም ለአካባቢው ተቆርቋሪነት ይኖራቸዋል ከሚል መነሻ የመነጨ ሊሆን ቢችልም አተገባበሩ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ እየፈጠረ ያለው ችግር በጣም ሰፊ ነው፡፡
በአስተማሪዎቹም ሆነ በተማሪዎቹ መካከል የሚታየው ሥር የሰደደ የዘረኝነት መንፈስ ተስፋን ከተቀበረበት ጥልቅ ጉድጓድ መንጥቆ በማውጣት እንደ ጉም ብን አድርጎ የሚያጠፋ ነው፡፡ ዘርን መሠረት አድርጎ የሚነሳ ማናቸውም ነገር የሚመራን ወደ ጨለማው ነው፡፡ ጨለማው ደግሞ ፊታችን ላይ ታይታ የነበረችውን የብርሃን ፍንጣቂ የሚያደግዝ፡፡ ጨለማው እንዲቀርበን እየተባበሩ ካሉት ውስጥ ከፍተኛው ሚና የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች ነው፡፡
ሐገራችን ካሏት ዩኒቨርሲቲዎች በአብዛኞቹ (ሙሉ ለሙሉ ለማለት ሁሉንም የማላውቃቸው በመሆኑ ነው) አስተማሪ ሆነው ከሚሰሩት ውስጥ በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተማሪዎቻቸውን ቋንቋቸውን መሠረት አድርገው የምዘና ውጤታቸውን ይሞላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ቋንቋቸውንና ዘራቸውን እንደመሣሪያ በመጠቀም ከመጡበት አካባቢ የሚመጡ ሴት ልጆችን ያባልጋሉ (ያባልጋሉ ማለት ስህተት ይመስለኛል፣ ምናልባት ይባልጋሉ ቢባል ድርጊታቸውን ይገልጸው ይሆናል)፡፡ ንፁህ ልብና እእምሮ ይዘው የመጡ ምስኪን ወጣቶችን የመመረዝ ሥራን ይሠራሉ፡፡
የዘረኝነቱ ጉዳይ ለመግለጽ የሚከብድ ነው፡፡ ምናልባትም ራሱን በቻለ ርእስ ሰፋ ብሎ ቢብራራ በርከት ያሉ ገጾች ያሉት ጽሑፍ ይወጣዋል፡፡ ትልቁ ጉዳይ የሞራል ልሽቀቱ ነው፡፡ አንድ መምህር ሊያስተምራቸው ፊት ለፊታቸው ከሚቆም ተማሪዎቹ ጋር አብሮ ሲጠጣና ሲጨፍር እያደረ፤ ሰክሮ አብሮ ሲንዘላዘል እየታየ ተስፋ ያለው ሰው ሆኖ በዚች አገር መንቀሳቀስ ከተቻለ ዓለም እጅግ ድንቅ ነገር ብላ ልትመዘግበው ይገባል፡፡
ምኑ ተነግሮ ምኑ ሊቀር እንደሚችል ማሰብ በራሱ ከባድ ነው፡፡ ማን ተወቅሶ ማን እንደሚቀር ግልጽ አይደለም፡፡ መንግሥት ተብየው ራሳችንን ችለን መቆም እንዳንችል ደጋፊ ጡንቻዎቻችንን እያሰለለ ጅማቶቻችንን ሲመዝ የሚውል ነው፡፡ የሃይማኖት አባት ተብየዎች አደገኛ የሚባሉ ወንበዴዎች እንኳን ሊሰሩት የማይችሉት ነውር ሲፈጽሙ እየታዩ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በራሱ የቆመበት የጠፋበት ይመስለኛል፡፡ የሚያስበው ስለሰውነት ሳይሆን ስለገንዘብ ብቻ ነው፡፡ እውቀት፣ እሴት ምናምን የሚባሉ ነገሮች አያውቅም፡፡ የሁለት አመት ልጁ ምን ዓይነት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ማየት እንዳለበት እንኳን አያውቅም፡፡ አሰቃቂ ትዕይንቶች ያሉባቸው ፊልሞችን ህፃን ልጁን አቅፎ የሚመለከት አባት ብዙ ነው፡፡

ምኑን አንስቶ ምኑን መተው ይቻላል? እስኪ የሚቻለን ከሆነ ብዙ ነገሮችን አብረን እናያለን፤ እናነሳለንም፡፡

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡