Tuesday, December 24, 2019

ቃሌን አጥፌያለሁ!

ውዴ ሆይ!

ቃል የገባሁትን ያኔ እንድንጋባ፣
ተሳስስበን ተሳስረን ቤት እንድንገነባ፣
የገባነውን ውል አጅቦን መሃላ፣
ትቼው ረስቼው ተካሁት በሌላ፤

ውድዬ ውዲቷ!

ለምን ሆነ ካልሽም ልብሽ ከታመመ ከገባሽ ትካዜ፣
ጥያቄ ከሆንሽ የቃሌ መታጠፍ ውሉን መሰረዜ፣
የኔ ማር!
የኔም ጥያቄ ነው ያንች የሆነው ሁሉ፣
የገመድ ቋጠሮ የተበተበ የማይገኝ ውሉ፣
መስቀለኛ መንገድ መሃሉ ላይ ጥሎ ድንግርግር አድራጊ፣
ሆኖብኛል እና ከግራ ወደቀኝ የሚያመላልሰኝ እንደዘሃ ዘጊ፣
በዋገምት የማይሽር ቁርባ ሠርቶብኝ ሕማምን ስቦብኝ ከነጥላ ወጊ፣
ነቀርሳ ሆኖብኝ ጣር ቢጠናብኝ እንጂ፣ ሌላ አልተካሁብሽም ፈጽመሽ አትስጊ፤

የኔ ውድ፣ ዓለሜ!

ዓለምን የሞላት ግሳንግሱ ሁሉ፣
አልጨበጥ ብሎ ቢጠፋብኝ ውሉ፣
ስለጋብቻችን ባስብ ባሰላስል ምን ብመታ መላ፣
በዛሬ አሻግሬ እያየሁ ሳወጣ ሳወርደው የነገን ሳሰላ፣
ነገ የሚያመጣው ያ ትንሹ ልጄ ያልተሟሸው ሸክላ፣
ሕማሙን ዐይቸው ተስፋዬ መንምኖ የእምነቴ ክር ላላ፤

እናልሽ የኔ ሆድ!

ላገባሽ ያልሁትን ቃሌን አጥፌያለሁ፣
ሐሳቤን ለውጬ ሌላ ሰው ሆኛለሁ፣
ጋብቻ አስጠልቶኝ ብቸኝነት ጥሞኝ ስላገኘሁ ለኔ፣
ሰመመን ውስጥ ነኝ ቀስቃሽ የማያሻኝ የሚሆን ከጎኔ፤

ስለዚህ ናፍቆቴ!

አልመጣም፣ ጋብቻችን ቀርቶ ውላችንም ፈርሷል፣
በጋራ ያቀድነው በኔ የግል ሕልም ከተተካ ከርሟል፤

ቢሆንም ግን ውዴ!

ማፍቀሬን አልክድም መወድድሽን አልረሳም፣ አይፋቅምና መቼም ቢሆን ከቶ፣
ስንቅ ስለሆነ የተመረገ ጠጅ፣ የመንፈሴ ቀለብ የጠጣሁት ጊዜ ትዝታው ተከፍቶ።

             ታመነ ቻላቸው
             14/04/2012

Wednesday, August 21, 2019

ገድለ እስከዚያው

         
"እኔ የተፈጠርኩት ሰዎችን ለማስከፋት ነው፤ ያስከፉኝን ለማስከፋት ነው፤ ፈጣሪንም ለማስከፋት ነው።" ይላሉ።  የነተበ ልብስ ለብሰው ጥንብዝ ብለው ሰክረው እየተንገዳገዱ ይራመዳሉ። ፊታቸው በማዲያት የተሸፈነ ነው። የፊታቸው ገጽታ ያሳለፉትን የጉስቁልና ዘመን ይተርካል።
"እስከዚያው ተመልከት እባላለሁ። የእያንዳንድሽን ገመና ፀሐይ ላይ አውጥቼ እንዳሰጣ ውክልና ያለኝ ብቸኛው ግለሰብ ነኝ" ይላሉ ምን ዓይነት ቀለም እንደነበራት እንኳን ለማወቅ በምታስቸግረው ኮዳቸው ከያዙት አረቄ እየተጎነጩ። አንዳንዴ የሚከተላቸው ግሪሳ አለ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ብቻቸውን መንተል መንተል ሲሉ ይታያሉ።
ወጣቶች፣ አዋቂዎችና ሽማግሌዎች ግን ይጠየፏቸዋል። ገና ድምጻቸውን "መጣ ደግሞ ይሄ ዓለም የረሳችው አምቡላም ሽማግሌ" ሲሉ ያማርራሉ። ይሄ ግን ለእስከዚያው ቁብ አይሰጣቸውም። "ያለበት ተጉላላበት"ን ይተርቱባቸዋል። "የረከሳችሁ ስለሆናችሁ፣ ያደፈ ማንነታችሁን ለመደበቅ በኔ ያደፈ ልብስ ታፌዛላችሁ። እድፋም ሁላ! ያደፈ ጭንቅላታችሁን ከቅርጭጭቱ አላቁት። ቅርጭጭታም ሁላ! ሃሃሃሃሃሃሃሃ!..." ይሉና ወንከር ወንከር እያሉትንሽ ይራመዳሉ።
ንግግራቸው ቢያሳርራቸውም ያሽካካሉ። እስኬው ሆዬ ዘውር ይሉና "ማክላላት ላህያ አመሉ ነው። የቀራችሁ መንከባለሉ ነው። ከዘዶቻችሁ የምትለዩት በሁለት እግር በመራመድ ብቻ ነው። በቀር ቁርጥ እነወሸን! ካካካካካካካካካ ....." ይሉና እርምጃቸውን ይጀምራሉ።
ደግሞ ተመልሰው በንዴት የጦዙትን ሰዎች ያሉ። እናም "እኔ የተፈጠርሁት ሰዎችን ለማስቀየም ነው። ፈጣሪንም ቢሆን!" ይላሉ። ተንደፋድፈው በጢማቸው ይደፋሉ። ትናንትም እንደዛሬው ነበሩ፤ ነገም እንደዚያው። ይሄው ነው የእስከዚያው ገድል ጉዞ።

Monday, February 11, 2019

መግባባት ይኖረን ዘንድ ምን እናድርግ? ምንስ እንሁን?

ከዐርባ አምስት (45) ዓመታት ቀደም ብሎ የጀመረው በሐገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ የጋራ አቋም መያዝን ሽሽት ዛሬ ላይ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሷል። የአንድ ሐገር ሰዎች ተብለን እንጠራ እንጅ እርስ በእርስ የምንተያየው እንደተለያዩ ሐገራት ዜጎች ነው። እንደተለያዩ ሐገራት ብቻም ሳይሆን ታሪካዊ ጠላትነት እንዳላቸው ሐገራት ዜጎች መተያየት ከጀመርን ውለን አድረናል።

ኢትዮጵያ የሚለውን ሥም በጋራ እንጠራበት እንጂ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ የምንጋራው አቋም የለንም። በአንድ ሐገር እየኖርን፣ አንድ የይለፍ ወረቀት (Pass Port) እየተጠቀምን፣ በአንድ መንግሥት ሥር እየተዳደርን፣ ወዘተ ... የጋራችን የምንለው እና የምንስማማበት ጉዳይ ግን የለንም። 

ይኸንን ከላይ ያነሳሁትን ነጥብ የሚያስረግጡ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። በርካታ የጥቁር ሕዝብ ሐገራትና ሕዝባቸው የነጻነት ፋና ወጊ አድርገው የሚያዩትን እና እንደድላቸው አድርገው የሚቆጥሩትን የዓድዋ ድል እንኳን ልንስማማበት አልቻልንም። የእነ እከሌ ድል ነው፤ የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ ... ዓይነት የውርክብ ሐሳቦችን እየተወራወርን መናቆሪያ አድርገነዋል። ያለፈውን የኛው ታሪክ ከምንማርበት ይልቅ መበሻሸቂያ፣ መነቋቆሪያ፣ መነታረኪያ እነና የጥል ግንብ ማቆሚያ በማድረግ ላለመግባባት ስንኳትን እንውላለን።

ቋንቋን ከመግባቢያነትና ከሐሳብ መግለጫነት ነጥለን የጥልና የብጥብጥ መሣሪያ አድርገነዋል። በቋንቆቻችን ውስጥ የተከማቹ እውቀቶችን በመጋራትና በማጋራት የበሰለ ሐገራዊ አመለካከት ያለው ማኅበረሰብ ከመገንባት ይልቅ የመለያያ አጥር እየሠራንባቸው አቅጣጫው ወዳልታወቀ አድራሻ እየነጎድን ነው።  በቋንቆቻችን ውስጥ የተቀበሩ እውቀቶችን እያወጣን የጋራ የሚባል ማንነት ለመሥራት ከመጣር ይልቅ ልጆቻችን እና ታናናሾቻችን የማይግባቡበትን መንገድ ለመፍጠር የእነገሌን ቋንቋ ማወቅ የለባችሁም በማለት በእንቁላል ውስጥ እንዳለ ሽል አፍነን ለማስቀረት እንታትራለን። 

በዚህ ሁሉ ጉዟችን መግባባት የማይችል ዜጋ ለመፍጠር ተሳክቶልናል። ከተጣባን የችጋር ደከከን የሚያላቅቀን መንገድ መፈለግን ደግሞ በሚያስደምም ሁኔታ ረስተነዋል። የሰው ልጅ ያለውን በነጻነት የመሰብና የመሥራት ተፈጥሯዊ ሥጦታ በመንጠቅ ሲዋጣልን ራሳችንንም ሆነ ማኅበረሰባችንን የሚለውጥና ከድህነት አረንቋ የመምዘዣ መንገድ ለመቀየስ ግን ወገቡን እንደተመታ እባብ እየተቅመደመድን  ነው።

ለመሆኑ እንደዚህ የሆንነው ለምንድን ነው? ከዚህ የሐሳብ ድርቅና ቆፈንስ መውጣት የምንችለው እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ነው? መውጫ መንገዱን ለመፈለግስ ምን ማድረግና መሆን ይጠበቅብናል? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እያነሳን መወያየትና መሟገት አስፈላጊ ቢሆንም ረስተናቸዋል። በመሆኑም እንደግለሰብ የሚታየኝና የሚሰማኝን በዚኽች ጦማር በተከታታይ ለማቅረብ በመሞከር የድርሻየን ለመወጣት ጀምሬያለሁ። መግቢያው ይኼው። ቀጣዮቹ ክፍሎችም ይቀጥላሉ።

Tuesday, January 29, 2019

የዘንበል ዘንበል ጉዞ የት ያደርሰናል?

የኢትዮጵያን ታሪክ ስናነብም ሆነ እንደየዕድሜያችን መጠን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገዛዝ እና ለገዥዎች የነበረውንና ያለውን ዕይታና አቀባበል መረዳት ከባድ አይሆንብንም። እኔም ባነበብሁት መጠንና በሕይወት ጉዞየ በታዘብሁት መጠን ጉዳዩን የቻልሁትን ያህል ለመረዳት ጥሬያለሁ። በኔ መረዳት መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሕዝብ የአገዛዝ ሥርዓትና ገዥዎችን በተመለከተ የነበረውና ያለው አቋም "ዘንበል-ዘንበል" ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው።

ዘንበል-ዘንበል ማለት ነፋስ በሚነፍስ ወቅት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትሎ ጎንበስ ማለትን፤ እንደገናም ደግሞ ነፋሱ አቅጣጫ ቀይሮ ሲመጣ ወደተቀየረው አቅጣጫ ማጎንበስ ነው። ይህ በተፈጥሯቸው ጠንካራ ያልሆኑ የሣር ዝርያዎች ባሕሪ ነው። ሣሮች ከመነቃቀል የሚድኑት የነፋሱን አቅጣጫ ተከትለው በመተኛት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብም የሣሮችን ተፈጥሯዊ ባሕሪ በመኮረጅ ከራሱ ጋር አላምዶና አዋድዶ የመጣው አገዛዝና ገዥ የያዘውን አቋም ተከትሎ እየተጓዘ የኖረና እየተጓዘም ያለ ነው። ከዚህ ባሕሪ ጋር መስማማቱንም "እንደንፋሱ አጎንብሱ" በሚል ምሳሌያዊ አነጋገር አስደግፎ የሕይወት መመሪያ እንዲሆን በማድረጉም የቀደሙትን ተከትሎ የሚመጣ አዲስ ትውልድ አገዛዝና ገዥዎችን በአዲስ መንገድ የሚያይበት መንገድ እንዳይቀርጽ ቀይዶ ይዞታል።

ዘንበል-ዘንበሉ ከሥርዓትም በላይ ግለሰብን ተመርኩዞ የተገነባ በመሆኑም አንድ ገዥ በተለየ መንገድ ሊመለክ ምንም አልቀረው እስኪባል ድረስ ለግለሰቡ ማጎብደድን ያስተማረና እያስተማረ ያለ ባሕሪ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም ምክንያት እንደ እንስሳ መንጋ ከፊት የቀደመው ገዥ የቀደደውን ቦይ ተከትሎ የሚፈስስ ኢ-ምክያታዊና ኢ-ተጠየቃዊ ግብስብስ አድርጎት አልፏል፤ እያለፈም ነው።

በዚህም ምክንያት ሥርዓት ገንብቶ የሚመጡ ገዥዎችን ሁሉ መምራትና መዘወር የሚያስችል መንገድ መቀየስ እንዳይቻል ሆኗል። በዚህም ምክንያት ሥልጣን የጨበጠውን ገዥ ባሕሪ ተከትለን የምንተምም ደመ-ነፍሳዊ መንጋ ሆነናል። የመጣው ሁሉ የቀደደልንን ቦይ ተከትለን የምንፈስ አስተውሎት የተሳነን ጥርቅሞች ሆነናል። የተለየ ዕይታ ያላቸውን የምንደቁስ፣ አንስተን እያፈረጥን ከመሬት የምንሰፋ ባለትንፋሽ ግዑዞችም ሆነናል።

የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን ድንብርብር እና በፍርሃት ቆፈን የተሸበብን፣ ከሥርዓት ግንባታ ይልቅ ግለሰባዊ ማንነት ላይ የምንንጠለጠል የጅምላ አስተሳሰብ ተጠቂ አድርጎናል። ሆኖም ግን ቀጥለንበታል። ዛሬም ከተቀደደልን ቦይ ባሻገር የማናይ አቅመ-ቢስ መንታሎች አድርጎናል። ራሳችንን በራሳችን የምናፍን ገራሚ ፍጡሮች አድርጎናል።

ሆኖም ዘንበል-ዘንበላችንን ለማቆም አልቻልንም፤ ወይም ለማቆም ፍላጎቱም ሆነ ፈቃዱ የለንም። ቀጥለንበታል። የት እንደሚያደርሰን ግን አናስብም። ግን ለመሆኑ ይህ የዘንበል-ዘንበል ጉዟችን የት ያደርሰናል?

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡