የመሸ
ቢመስልህ የገባ ብርሃን የወጣ ጨለማ፣
ተስፋህ
ተመናምኖ ብርክ ቢሆን ጭንቀትህ ቢሰማ፣
ኑሮህ
ቢያስጎነብስ የእንብርክክ ቢያስጊዝም ግስም እያረገፈ፣
ተረት
ቢያስተርትህ “ተንጋለው ቢተፉ…” ቢያሰኝህ ይህስ ቀን ባለፈ፣
ከድጡ
ለማምለት እያውተረተረ መልሶ እየጣለህ ቢከትህ ከማጡ፣
እጅ አትስጠው
ለእሱ የማይቀር ነው እና ነገ መለወጡ፣
በአለበሰህ
ጭቃ ለራሱም በተራው ገብቶ መላቆጡ፣
ሕጉ በመኾኑ
የተፈጥሮ ዑደት፣ ቢዘገይም ለውጡ፣
ድል መንሳት
አይቀርም በሕወት ጉዞ ላይ ተስፋ ካልቆረጡ፡፡
እናልህ
ወንድሜ፣
በዛሬ
ላይ ትናንት ጠል እንዳይጥልበት፣
ደይኖ
እንዳይይዘው ተክቶት ነግሦበት፣
ነገን
አጠንዝሎ አክስሎት እንዳያልፍ፣
በእውቀትህ
ከመራኸው ዛሬ ሳይዛነፍ፣
በእናት
ማባበያ ልጅን መደለያ በእነእሰጥሃለሁ ኋላ “ጉዳጉዶ”፣
ካልተደለለ
ሆድ ሚዛንን አስቶ በጥቅም ለውጦ ኅሊናን አስክዶ፣
የማታ
የማታ ማሸነፍ አይቀርም ማየት ጠላት ወድቆ፣
ከቁዘማህ
መውጣት በመንሰቅሰቅ ፋንታ መገኘት ፈንድቆ፡፡
ስለዚህ
ወንድም ሆይ፡-
ሳንካ
የሆነብህ መንገድ እየዘጋ፣ ግድግዳው ይወድቃል ተንኮታኩቶ ደቅቆ፣
መንገድህ
ይጠራል ያንተ ጥረት ውጤት ከብሮ ሊታይበት ሊቆምበት ደምቆ፣
ጨለማው
ይሸሻል በወጋገን ጨረር ጎኑ እየተወጋ ዛል ጥንዝል ብሎ፣
ተስፋህ
እሸት ኾኖ ጎመራል የበለጠ ደምቆ የነገን ድል አዝሎ፣
እናማ፣
ዛሩህን
ከያዝኸው ተጠንቅቀህለት አክብረኸው ከኖርህ የሕይወትን ሥራ፣
ነገህ
ይክስሃል ወይን ይሆንልሃል የሕይወት ምሰሶ ጣፋጭ የሚያፈራ፡፡