Monday, February 11, 2019

መግባባት ይኖረን ዘንድ ምን እናድርግ? ምንስ እንሁን?

ከዐርባ አምስት (45) ዓመታት ቀደም ብሎ የጀመረው በሐገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ የጋራ አቋም መያዝን ሽሽት ዛሬ ላይ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሷል። የአንድ ሐገር ሰዎች ተብለን እንጠራ እንጅ እርስ በእርስ የምንተያየው እንደተለያዩ ሐገራት ዜጎች ነው። እንደተለያዩ ሐገራት ብቻም ሳይሆን ታሪካዊ ጠላትነት እንዳላቸው ሐገራት ዜጎች መተያየት ከጀመርን ውለን አድረናል።

ኢትዮጵያ የሚለውን ሥም በጋራ እንጠራበት እንጂ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ የምንጋራው አቋም የለንም። በአንድ ሐገር እየኖርን፣ አንድ የይለፍ ወረቀት (Pass Port) እየተጠቀምን፣ በአንድ መንግሥት ሥር እየተዳደርን፣ ወዘተ ... የጋራችን የምንለው እና የምንስማማበት ጉዳይ ግን የለንም። 

ይኸንን ከላይ ያነሳሁትን ነጥብ የሚያስረግጡ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። በርካታ የጥቁር ሕዝብ ሐገራትና ሕዝባቸው የነጻነት ፋና ወጊ አድርገው የሚያዩትን እና እንደድላቸው አድርገው የሚቆጥሩትን የዓድዋ ድል እንኳን ልንስማማበት አልቻልንም። የእነ እከሌ ድል ነው፤ የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ ... ዓይነት የውርክብ ሐሳቦችን እየተወራወርን መናቆሪያ አድርገነዋል። ያለፈውን የኛው ታሪክ ከምንማርበት ይልቅ መበሻሸቂያ፣ መነቋቆሪያ፣ መነታረኪያ እነና የጥል ግንብ ማቆሚያ በማድረግ ላለመግባባት ስንኳትን እንውላለን።

ቋንቋን ከመግባቢያነትና ከሐሳብ መግለጫነት ነጥለን የጥልና የብጥብጥ መሣሪያ አድርገነዋል። በቋንቆቻችን ውስጥ የተከማቹ እውቀቶችን በመጋራትና በማጋራት የበሰለ ሐገራዊ አመለካከት ያለው ማኅበረሰብ ከመገንባት ይልቅ የመለያያ አጥር እየሠራንባቸው አቅጣጫው ወዳልታወቀ አድራሻ እየነጎድን ነው።  በቋንቆቻችን ውስጥ የተቀበሩ እውቀቶችን እያወጣን የጋራ የሚባል ማንነት ለመሥራት ከመጣር ይልቅ ልጆቻችን እና ታናናሾቻችን የማይግባቡበትን መንገድ ለመፍጠር የእነገሌን ቋንቋ ማወቅ የለባችሁም በማለት በእንቁላል ውስጥ እንዳለ ሽል አፍነን ለማስቀረት እንታትራለን። 

በዚህ ሁሉ ጉዟችን መግባባት የማይችል ዜጋ ለመፍጠር ተሳክቶልናል። ከተጣባን የችጋር ደከከን የሚያላቅቀን መንገድ መፈለግን ደግሞ በሚያስደምም ሁኔታ ረስተነዋል። የሰው ልጅ ያለውን በነጻነት የመሰብና የመሥራት ተፈጥሯዊ ሥጦታ በመንጠቅ ሲዋጣልን ራሳችንንም ሆነ ማኅበረሰባችንን የሚለውጥና ከድህነት አረንቋ የመምዘዣ መንገድ ለመቀየስ ግን ወገቡን እንደተመታ እባብ እየተቅመደመድን  ነው።

ለመሆኑ እንደዚህ የሆንነው ለምንድን ነው? ከዚህ የሐሳብ ድርቅና ቆፈንስ መውጣት የምንችለው እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ነው? መውጫ መንገዱን ለመፈለግስ ምን ማድረግና መሆን ይጠበቅብናል? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እያነሳን መወያየትና መሟገት አስፈላጊ ቢሆንም ረስተናቸዋል። በመሆኑም እንደግለሰብ የሚታየኝና የሚሰማኝን በዚኽች ጦማር በተከታታይ ለማቅረብ በመሞከር የድርሻየን ለመወጣት ጀምሬያለሁ። መግቢያው ይኼው። ቀጣዮቹ ክፍሎችም ይቀጥላሉ።

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡