ዐይንሽ ደምቆ የሚታየኝ ካረፍኩበት የሚጠቅሰኝ፣
የሚጠራኝ
ልቤ ባዶ፣ ዐይኔ ምኞት ስለያዘው መንፈሴን ስለራበኝ
እንጂማ
አንቺን እንድጠላሽ ከምውድሽ በላይ ነበረኝ ሰበቡ
ሕማም ቢሆንብኝ በደልን ማመንዠክ፣ ደጋግሞ ማሰቡ
እርም ይረመኝ ብየ አራግፌ ጣልኩት
አንቺን እንዳላጣ አምርሬ ጠላሁት
ታዲያስ
አንቺን ትቼ
ፍቅሬን ተጣልቼ
ውዴን ረስቼ
ፍቅርሽን ሸሽቼ
መግቢያዬ የት ሊሆን የትአባቴስ ልደርስ
ምንስ እያሸተትኩ ምንስ ልተነፍስ
መዓዛሽን ርቄ
መውደዴን ደፍቄ
ሳይሽ መደንበሩን መርበትበት መራዱን ለማን አቀብዬ
ብስክስክ ገላሽን ተሰባሪ መሳይ ወዴት አስቀምጬ
ማን ይጠብቅ ብዬ፡፡