Wednesday, June 1, 2016

ሰው ነበር!




በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ማረሻና ድግር፣ ሞፈርና ቀንበር
ተሸክሞ ወጥቶ የሚታገል ካፈር
ማጭድና መንሹን ማርገቢያ ላይዳ
ችግሩን ሸክፎ ከትቶ በአኩፋዳ
ጋራውን የወጣ ቁልቁል የወረደ
ለግዜር እንግዳው ሲል ጠቦቱን ያረደ
የደግነት አባት፣ የልግስና እናት መሆኑን ያሳየ
ዕውቀትን ለማግኘት ማጥን የቀመሰ አሳር ችግር ያየ
የጥንካሬ ምንጭ የጀግንነት አርማ
ሐሩር ተቋቁሞ ጭንጫውን ያለማ
በቆንጥር በእሾሁ በጋሬጣው አልፎ
ድንበር የጠበቀ ለዘብ ተሰልፎ
መንገድ የጠረገ በዋሻ ቀዳዳ ማለፊያ ያመጣ
ሊወር ሊበርዘው የዘመተበትን መድረሻ ያሳጣ
አርበኛ መልምሎ ፈትኖ አንጥሮ ያወጣ
ጀግናስ ነበር ባገር የሚታወስለት ከውስጡ ያላጣ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
መልካም ሰው ያፈራ መልካም የተባለ
ምስክር ያላጣ ማንነቱን ገፍቶ ወርውሮ ያልጣለ
በፍልፈል ኵይሳ በቀበሮ ጉድጓድ ገብቶ ተወሽቆ
ጥበቡን ያሳየ ዕፁብ ሕንፃ ሠርቶ አለትን ፈቅፍቆ
መከራን ተሻግሮ ጋሩን አሳልፎ ደስታን ያነጠፈ
የቆሸሸ ለብሶ የሚበላው ቢያጣም ውስጡ ያላደፈ
ውሽንፍር ወጀቡን በጥበብ ያለፈ
ባለደማቅ አርማ ኰኰብ የለበሰ
አካሉ ያነሰ ልቡን ያነገሠ
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ሀ ብሎ ጠንቁሎ አንድ ሁለት እያለ ከድንጋይ ቆልሎ
ከካብ የዘለለ በግርማው ያማረ ትልቅ ሐውልት ላይ ሰንደቅ አሰቅሎ
በልቡ ባሕር ላይ ባንሳፈፈው ጀልባ መቅዘፍን ተምሮ
ከባሕሩም ወዲያ ከባሕሩ ወዲም ያገኘውን ሁሉ ቀምሞ መርምሮ
ሞት ብቻ ሲቀረው ሁሉን አሸንፎ
ያለፈ ሰው ነበር በሕሊናው አርፎ፡፡
       በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
      በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
በ ብሎ ደርድሮ በበገና ክሮች መንፈሱን አድሶ
ክራሩን ከርክሮ መሰንቆ ገዝግዞ አንጀቱን አርሶ
በሙዚቃው ቃና በጭፈራው ድምቀት በእልልታው ታጅቦ
ላለመደራረስ እየተማማሉ፣ ቆርጠው የነበሩን ያዋለ ሰብስቦ
ባለጎፈር ጀግና ባለለምድ ጎስቋላ
ባለበረት ንብረት ባለዕዳ መንታላ
ባለዐደራ ሆኖ ይልሰው ሳይኖረው ዐደራ ያልበላ
አጥር ተሸካሚ ሰዋሰው ደገሌ ባለሁለት ባላ
ችንካርም ምሰሶ ወጋግራ እየሆነ ጎጆ የቀለሰ
በጎረቤት ንጣት ውድቀት የቆዘመ እንባ ያለቀሰ
ቁስሉ ሳይጠግለት ሕማሙ ሳይለቀው ገመምተኛ ሳለ
የሐገሩን ጥሪ በፍርሃት በክህደት በእብለት ያልጣለ
በተፈለገበት መስክ ቀድሞ የተገኘ
ባልተማረ አንደበት ቅኔ የተቀኘ
የሆድ ነገር ብሎ ለሆድ ያልተገዛ ለሆድ ያላደረ
እንደ ልቡ ፈቃድ በሕሊናው ምሪት የጣረ የጋረ
ባለ-ስም ስም-አልባ ባለክብር ክብር ያጣ
ሐብት ሞልቶ ተርፎት ችግር ያራቆተው ቀኝ እጁ የነጣ
በነጣ ቀኝ እጁ ልሒድ ልሒድ ያለ ግራውን የቀጣ
ፍፁም ፈውስ ያገኘ አእምሮው ያረፈ ከሕሊና ቁጣ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
በፈዘዘ ሌሊት ብርሃን ፈንጥቆ ጨለመ ገፋፊ ጭላንጭል ፈንጣቂ
ከአንበሳ መንጋጋ ስጋ ያስለቀቀ ከነብር ጥፍሮች ሥር ሙዳ ተናጣቂ
እኔ ከሞትኩ ብሎ ሰርዶ ያልነቀለ
አሻራ የሚሆን ባለግርማ ሐውልት በጁ የተከለ
ሳይንስ ያላወቀ ሳይንስ ያረቀቀ
ጥበብ ያነገሠው በጥበብ የላቀ
ክክፋት ውቅያኖስ በደግነት ታንኳ ተንሳፍፎ የወጣ
ከመደንቆር ባሕር በዋና መፍጨርጨር አምልጦ የመጣ
በጨለማ ዋሻ አተምትሞ ሮጦ መንገድን የመራ ተስፈንጥሮ ወጥቶ
በእርዛት ዘመኑ ወገኑን ያልተወ ክብር ያለበሰ አጣፍቶ ድሪቶ
ችጋር ቸነፈሩን በማጎንበስ አልፎ ለጭቆና ቀንበር ያላጎነበሰ
መገዛትን ሸሽቶ መግዛት ያልመረጠ ፍርድ ያላስነከሰ
ጨለማ ሰባሪ ተወርዋሪ ኰኰብ ጅራት ያበቀለ ለእንቅልፍ ያልታደለ
መታፈን ያልገታው የጠቆረን ሰማይ በብርሃን መስመር እኩል የከፈለ
ወቀሳና ትችት ተንኰልና ሸርን ዐይቶም እንዳላየ ሰምቶም እንዳልሰማ
በደግ! ያለፋቸው መንገድ የጠረገ ያልተወላገደ ያረቀ ጠማማ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
ረግረጉን አልፎ ከትልቅ ጋራ ሥር ጎጆ የቀለሰ
ያረጀ፣ የወደቀውን ቤት መልሶ ያቆመ በደሙ ያደሰ
ለቆመለት ጉዳይ አንገቱን የሰጠ ደሙን ያፈሰሰ
በጽናት ያደረ ፈተና ያልጣለው እ! ብሎ ካንጀቱ ውስጡ ያለቀሰ
መንፈሱ ያልላመ ክንዱ ያልደቀቀ
ነውር ያላሸነፈው ክብሩ ያልወደቀ
ወንድሙን እህቱን ሕዝቡን ያልሰረቀ
ወገንማ ነበር ራሱን አዋርዶ ሐገር የጠበቀ፡፡
በድንቅ ተጋድሎ አሻራ ያኖረ፣
በሑባሬ ገመድ ሐገርን ያሰረ፡፡
11/09/08
አርባ ምንጭ፣ ሲቀላ፡፡

 እኔ የማወራት የእርሷ ጆሮ ሲደርስ መልኩን እየሳተ እየተቀየረ፣ ከማፋቀር ይልቅ እኛን ከማዋደድ ጥል ፈጣሪ ኾነን እያጠራጠረ፡፡